Search
  • gyisma83

መቸንከሪያ መሃል

መቸንከሪያ መሃል እያጣን ነው

ድሮ አባቶቻችን ዳር ድንበር ሲደፈር፣ ጦራቸውን ሰብቀው ጋሻቸውን አንግበው ወደ ተደፈረው ድንበር ይተማሉ፡፡ ዳር ሲደፈር፣ መሃል ዳር ይሆናል ይሉ ነበር፡፡ ዛሬ በአገራችን የሕግ የበላይነት በመጥፋቱ የሩቁ፣ የዳር ዳሩና የመሓሉ የሚባል የለም፡፡ የዘር የሃይማኖትና የቋንቋን ልዩነት ምክንያት ያደረጉ ጽንፈኞች በሚያካሂዱት ሁከት አገሪቷ በሙሉ በመናወጥ ላይ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ጽንፈኞች ሰላም የሰፈነበት መሰባሰቢያ መሃል ሊያሳጡን እየሰሩ ነው፡፡ ይህን ቀውስ የፈጠሩትን ጽንፈኞች መንግሥት በጅምሩ እርምጃ ባለመውሰዱ እንደቋያ እሳት ከቦታ ቦታ እየዘለሉ አገሪቷን ትልቅ ቀውስ ውስጥ እየከተቷት ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሁከቶች እየፈነዱ ገዳቢ ኬላዎች እየተጣሉ የንፁህ ዜጋዎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ቤተክርስቲያኖችና መስጊዶች ተቃጥለዋል፣ ንብረት ወድሟል፤ ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል፣ ሕዝብ ሰላም አጥቷል፣ ጸጥታ ደፍርሶ ስጋት ነግሷል፡፡ ሰላም አለበት የምንለው መሓል እንኳ የለንም፡፡ ሕዝባችን የመንግሥት ያለህ እያለ ነው፡፡

ይህ ሃይማኖትንና ዘውግን ተጠቅሞ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ተግባር ከቀጠለ ማእከላዊው መንግሥት የሆነው የፌደራሉ መንግሥትን እጅና እግር የሚያሰልል (ፓራላይዝ የሚያደርግ) ቀውስ ነው የሚሆነው፡፡ ጽንፈኞች በአሁኑ ጊዜ እየሰሩ ያለውም ማእከል ለማሳጣት ነው፡፡

ከመንግሥት ውጭም ሆኑ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ጽንፈኞች ሃይማኖትንና ዘውግን ምክንያት አድርገው አንዱን ወገን በሌላ ላይ ሲያነሳሱ፣ ለእርስ በእርስ እልቂት ሲጋብዙ እየሰማን ድርጊቱም ሲፈጸም እያየን ነው፡፡ እነዚህን ኣይነት አገር አፍራሾች በሕግ ፊት አቅርቦ ተገቢ ቅጣታቸውን ከማሰጠት በቀር ሌላ አማራጭ ሊኖር አይገባም፡፡ በመንግሥት በኩል የተያዘው ግን በትእግስት ስም ማባበልና መለማመጥ ሆኗል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ጽንፈኞችን የበለጠ የሚያደፋፍራቸው እንጅ ከአጥፊ ተግባራቸው እንዲታቀቡ የሚያደርጋቸው አይደለም፡፡ እነዚህ ጽንፈኞች ዜጎችን በእኩልነት የማየት ብቃት ካለመኖር አልፈው ሌላውን የማግለልና የማጠልሸት አባዜ ውስጥ የተነከሩ ናቸው፡፡ ለምን? ስሌታቸው የተሰራበት ድርና ማግ ጥላቻ ስለሆነ፡፡

የክልሎችም ሆኑ የፌደራል መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አልቻሉም፡፡ በቅርቡ በኦሮምያ ክልል ውስጥ በዜጎች ላይ የተፈጸመው አሳፋሪና አሰቃቂ ድርጊት ዘግንኖናል፡፡ ይህን አሰቃቂ ድርጊት የፈጸሙ ሁሉ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ የመንግሥት ግዴታና ሃላፊነት ነው፡፡ ዜጎችን የገደሉ፣ የእምነት ተቋማትን ያቃጠሉ፣ ንብረት ያወደሙና ያፈናቀሉ፣ እና በዚህ ድርጊት በተለያየ ደረጃ የተሳተፉ ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ የኦሮሞ ክልል መንግሥትም ቢሆን በውስጡ ያሉትን ዜጎች ሰላም ማስጠበቅ ያልቻለው ስለአቃተው ብቻ አይደለም፤ መዋቅሩ የፖሊስ ሃይሉን ጨምሮ ያልጸዳ በመሆኑም ነው፡፡ በተለያየ የእርከን ደረጃ በሃላፊነት የተቀመጡ ጥላቻን የሚሰብኩ ሹሞች፣ የእርስ በእርስ ግጭት ለማስነሳት ሌት ተቀን የሚሰሩ የሚዲያ ድርጅቶች ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ሁሉም የክልል መንግሥታት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ግዴታቸው ሆኖ ሳለ የመንግሥታቱ አውታሮች ፖሊስንና መከላልከያን ጨምሮ ጽንፈኞች ጥፋት ሲያደርሱ እንደ ታዛቢ ቆሞ ማየት ከተባባሪነት ያስቆጥራል፡፡ የፌደራሉ መንግሥትም ይህን በቸልተኝነት መመልከት በውስጡ ያለበትን ችግር ያመለክታል፡፡

ዛሬ ሕዝባችን የሕግ የበላይነት ለማስከበር መንግሥት ቆራጥ እርምጃ እንዲወሰድ ይፈልጋል፡፡ ባዶ የቃላት ጋጋታ አይደለም የሚፈልገው፣ ወይንም አስሮ የመፍታት ማስመሲያ እርምጃዎችን አይደለም የሚጠብቀው፣ በየቦታው በጽንፈኞች የሚለኮሱ እሳቶችን ዛሬውኑ ማጥፋት አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው፡፡ የፌደራሉ መንግሥት እራሱን ከተለያዩ ጽንፈኞች አጽድቶ ማእከላዊነቱን በማጽናት፣ አድልኦ የማይታይበት የሁሉም መንግሥት እንዲሆንና ሰላም እንዲሰፍን እንዲያደርግ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

በዚህ ሁከት ለጠፉት ዜጎች ሁሉ የመረረ ሃዘናችንን እየገልጽን፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንመኛለን፡፡

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር፡፡

ጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት

0 views
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin