Search
  • gyisma83

‘እርስት በሺ ዓመቱ፣ ለባለቤቱ’

‘እርስት በሺ ዓመቱ፣ ለባለቤቱ’

ባለፉት ወራት ልብ አልነውም አላልነውም፣ በሴራ ውስጥ የኖረችው አገራችን በሴራ ውስጥ እንደምትኖር ሁኔታዎች ሊያስታውሱን ችለዋል። አገራችን፣ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተጎነጎኑባትን ሴራዎች እየበጣጠሰች፣ የደፈሯትን ጠላቶችም እያሳፈረች መልሳለች። እንድ ከምትታወቅባቸው እዎንታዊ መለኪያዎች አንዱ በውስጥ ያለውን የእኔ ልግዛ-እኔ ልግዛ የእርስ በእርስ ግጭትን ወደ ኋላ በማድረግ በጋራ ጠላት ላይ መረባረብን ነው። ለዚህም የጉንዴት እና የጉራዕ፣ የአድዋ፣ የማይጨውና ሌሎች ጦርነቶች የቅርብ ጊዜ ምሳሌዎች ናቸው።

ይህን ስንል ደግሞ በሌሎች ጊዜያት የእርስ በእርስ ጦርነቶቻችን ምክንያት ያደቡ ጠላቶቻችን በአገራችን የቆዳ ስፋት መቀያየር ላይ ተጽእኖ አልነበራቸውም ለማለት አይደለም። በፖለቲካ፣ በአካባቢ የግዛት ይገባኛል፣ በሃይማኖት ምክንያት ያኮረፉ ወገኖቻችንን በማባበልና በመጠቀም አገራችን ለማፍረስ ከመጣር አርፈው አያውቁም። እንዲያውም ሁልጊዜ አድብተው የሚጠብቁት ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ነው። ዛሬም በአገራችን ውስጥ የሰፈነውን አለመረጋጋት በማየት ለማጥቃት አሰፍስፈዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት በዜና አውታሮችና በየመድረኩ የአባይ ወንዝ የባለቤትነት ጥያቄ ያዘለ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአባይ ለመጠቀም የሕዳሴ ግድብን ያለማንም እርዳታ በራሷ አቅም ብቻ በ2011 ዓ ም መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ግብጽና መሰሎቿ አነጣጥረውባታል። ከተራሮቿ የፈለቀውን አባይን የምንቆጣጠረው እኛ ብቻ ነን በሚል ኢትዮጵያ ያልተወከለችበትን የቅኝ ገዥዎች ስምምነት በመንተራስ እብሪት የተሞላበትና ዛቻን የተቀላቀለ ክርክር በማቅረብ፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ እንዳትሆን ግብጽ ትልቅ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ነች። ግብጽ ኢትዮጵያን በሰሜን በምሥራቅና በምዕራብ ጦርነት ከፍታ አባይን ለመቆጣጠርና ኢትዮጵያ አቅም እንዳትገነባ እንደፈለጋት የምትገፋት ደካማ አገር ለማድረግ ስትጥር መቆየቷ ታሪካችን ይመሰክራል። አሁንም በ21 ኛው ምዕተ ዓመት ይህን የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ እየገፋች ነው። ለዚህም አንዳንድ የአረብ አገሮችን አሰልፋለች። በየአህጉሩ እየዞረች የፖለቲካ ዘመቻም በማካሄድ ላይ ነች ። የአሜሪካን መንግሥት አደራድሩኝ ብላ በመጠየቅ ኢትዮጵያ የማትስማማበትን ስምምነት እንድትፈርም ተጽእኖ እያሳደረች ነው።

ስለሆነም፤

1/ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷ ላይ በሚነሳ ማንኛውንም ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ መቀበል አይኖርበትም። አባይ አንድ ባለቤት ይኑረው አንልም እንጅ ይኑረው ከተባለ ማን ወለደውና!

2/ ኢትዮጵያ አገር ተሻጋሪ ወንዞችን በሚመለከት ዓለም አቀፋዊ (ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ አየር እና የትምህርት ኮንፈረንስ (UNCED)) ስምምነቶችን እንደምታከብር ሁሉ ግብጽም ይህ ግዴታ አለባት ። ሌሎችም ተፋሳሽ አገሮችም እንዲሁ። የጋራ ተጠቃሚነትና የጋራ ቁጥጥር መኖር ግዴታ ነው።

3/ የጋራ ወንዛችንን ሁለ-ገብ አውድ (echo system) መጠበቅ የሁሉም ተፋሳሽ አገሮች ግዴታ ነው። ይህን ሁለ-ገብ አውድ ለመጠበቅ አብዛኛውን ወሃ እና ለም አፈር የምታበረክተው ኢትዮጵያ እንደ ግብጽ ዓይነት ዋና ተጠቃሚ አገርን ሁለገብ አውዱን ለመጠበቅና ለማሻሻል የምትጠይቀው ማካካሻ ሊኖር ይገባል።

4/ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጣልቃ ገብ የሆኑ ድርጅቶችንም ሆነ መንግሥታት ከመቃወም መቆጠብ የለበትም። በተገኘው መንገድ ሁሉ የማያሻማ እምቢተኝነትን ማሳየት አለበት። የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት እጅ ጠምዝዞ ኢትዮጵያ ያልፈለገችውን ስምምነት እንድትፈርም የሚያደርገውን ግፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ መቃወም አለበት።

5/ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ አገሮች በድርድሩ እንዲሳተፉ ኢትዮጵያ መጠየቅ ይኖርባታል። የአፍሪቃን ጉዳይ አፍሪቃውያን ሊፈቱት ሲገባ ለግድቡ ሥራ ገንዘብ አላበድርም ያለ አካል አደራዳሪ መሆን እይገባውም።

6/ በትንንሹ ስንናኮር ትልቁን አገራዊ ጥቅምና ፀጥታ እንዳናጣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካም ሆኑ የሌላ አይነት ድርጅቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከግብጽ ጋር ምንም ዓይነት ግኙነት ማድረግ የለባቸውም። ግንኙነት እንዳለው የተረጋገጠበትን ድርጅት ወይንም ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክህደቱን ተመልክቶ አንቅሮ መትፋት አለበት።

7) የኢትዮጵያ መንግሥት የግድቡን ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ ይኖርበታል። የግብጽ ሕዝብ ከዳር እስከዳር በጉዳዩ ያገባኛል ብሎ ሲሳተፍ ከቀን ጉርሱ ቀንሶ ግድቡን የገነባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዩ ሊደበቀው አይገባም።

8) በውጭ የምንኖር ለአገር ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውን በያለንበት ለሚገኙት የተመረጡ የህዝብ ተወካዮችን ኮንግሬስሜን/ሴናተሮችን ኢትዮጵያ የምትከተለውን አለማቀፋዊ የአገር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሃዊ አጠቃቀምን ተመርኩዞ የሚሰራውን የግድብ ሥራ ሂደት ለማስናክል የተሄደበትን ጣልቃ ገብነት እንዲረዱና ጫና እንዲያደርጉ ማሳሰብ።

በአባይ ላይ ባለን ተፈጥሮአዊና ሕጋዊ መብቶቻችን ላይ አንደራደርም፤

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር።


0 views
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin