Search
  • gyisma83

የወሰኑ ጉዳይ

ሚያዚያ 28 2012 (5/5/2020)

የወሰኑ ጉዳይ

“የነገር ትህትና ያስረታል፣ የበትር ትህትና ያስመታል”

ከሱዳን ጋር ያለው የወሰናችን ጉዳይ ዛሬም እንደትናንትናው እና እንደዚያ ቀደሙ ያለ እልባት ተንጠልጥሎ ቆይቶ የግጭት አፋፍ ላይ አድርሶናል። ባለፉት ሁለት ወራት የሱዳን የመከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ስር በቆዩ ከሁመራ እስከ ቋራ በተዘረጉ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ድንበር ተሻግረው ወታደሮቻቸውን አስፍረው ምሽግ እየሰሩ ናቸው።

በጎንደር ነገስታት የግዛት ዘመን፣ ዛሬ የምንነግገርባቸው ቦታዎች ሁሉ መሃል ነበሩ። በዚያን ጊዜም ሆነ በኋላ ለወሰን ማስከበር ሳይሆን ለማስገበር ጦርነቶች ተካሂደዋል። ከዚያም በኋላ የደምቢያው ገዥ ደጃዝማች ክንፉ የዋድ ካልታቡ (Wad Kaltabu)ጦርነት አሸናፊ ሆነው አስገብረዋል። በ1848 አጼ ቴዎድሮስ ግዛት ለማስመለስ የግብጽንና የቱርክን ጦር ተዋግተዋል። አረቦች የአባቶቻችንን መሬት ይልቀቁ። ወሰናችን እስከ ጥቁርና ነጭ አባይ መገናኛ ነው ብለው ነበር። እንደ ኢ አ በ1875 ጉንዲት ላይ በ1876 ጉራዓ ላይ አጼ ዮሃንስ ያካሄዷቸው ጦርነቶችና የተገኙት ድሎች የዚሁ ክፍል ሁነው መታየት ያለባቸው ናቸው። የጎንደር በድርቡሾች መቃጠልና አጼ ዮሃንስ የወደቁበት የ1889 ጦርነትም ከዚሁ ዝርዝር የሚገቡ ናቸው። በ1890 እንግሊዞች ሱዳንንና ግብጽን አቀናጅተው መግዛት ከጀመሩበት ወቅት ጀምሮ አጼ ምኒልክ ከእንግሊዞች ጋር አያሌ ድርድሮችን እንዳካሄዱ በታሪክ ዘንድ ተመዝግቧል። የተቀበሏቸውና ያልተቀበሏቸው ነበሩ ካልተቀበሏቸው ውስጥ አንዱና አወዛጋቢው የሻለቃ ግዌን መስመር ነው። የግዌን መስመር የተባለው በወረቀት ላይ ያስቀመጠው መስመርም (ካርታ) ሆነ መሬት ላይ ያደረጋቸው በኢትዮጵያ በኩል ማንም ያልተወከለበትና በተናጠል በአንድ ወገን የተፈጸመ እንጅ ኢትዮጵያ በምንም መልኩ የተሳተፈችበትና የተተስማማችበት አልነበረም።

ይህ የወሰን ጥያቄ በንጉሥ ሃይለ ሥላሴም ጊዜ ተነስቶ ነበር። ንጉሱ ከሁመራ እስከ ቋራ መሬት ቆርሰው ለሱዳን ሊሰጡ ነው ተብሎ በጎንደር የሕዝብ እንቅስቃሴን አስነስቶ የቅስቀሳ ወረቀቶች በጎንደር ከተማና በአካባቢው ተበተኑ። አገር ወዳዶች ታጥቀው ጫካ ገቡ። በፓርላማ ውስጥ የጎንደር ክፍለ አገር ተወካዮች ፓርላማ ውስጥ ጥያቄውን አንስተው ለድብድብ ያበቃ ውዝግብ ተፈጠረ። በእነዚህ ምክንያቶች የተፈጠረው ውዝግብ ጉዳዩ እንዲያንቀላፋ ሆነ። ምስጋና ለጎንደር ሕዝብ እንቅስቃሴና እንዲሁም በፓርላማ ውስጥ ለረዷቸው አባሎች።

ሱዳን በደርግ ጊዜም ይህንኑ ጥያቄዋን አንስታ ሰሚ አላገኘችም። ደርግ በ1975 የአካባቢውን አስተዳደርና ሕዝብ ጠይቆ ኮሚቴ አቋቁሞ አስጠና። ምንም በጦርነቶች ቢዋከብም የኮሚቴውን ውጤት በመቀበል ታሪካዊ ወሰናችንን እናስከብራለን ብሎ ዘግቶት አለፈ።

በ1983 የደርግ መንግሥት ወድቆ ወያኔ ስልጣን ሲጨብጥ ሁኔታው ተቀየረ። በታሪካችን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጠላት ጋር የሚያብርና የራሱን አገር መሬት ለባእድ አስልፎ የሚሰጥ፣ በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ጠላት የሚወግን መንግሥት መጣ። ይህን የውስጥ ድጋፍ ያገኘው የሱዳን መንግሥት ተዳፈረን። ደፍረውት የማያውቁትን የኢትዮጵያ የቀረጥ በር የነበረውን ልጉዲን ገብተው ያዙ። በ1984 ዓ ም ጦር አሰፈሩ። ገበሬው ጮኸ። እንዲወጡ ሲጠየቁም፣ ሱዳኖች አንወጣም አሉ። ይህ በእንዲህ እያለ በ1987 ከሱዳን የመጡ ነፍሰ ጋዳዮች ሙባረክን ለመግደል ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀረ። በዚህ ምክንያት ሁለቱ መንግሥታት በመጣላታቸው የኢትዮጵያ መከላከያ በ 3 ቀናት ጦርነት የሱዳንን ወታደሮችን ገፍቶ አስወጣ። የኢትዮጵያ ገበሬዎችም ተመልሰው እስከ 1992 በይዞታቸው ቆዩ። ሰላም ሆኖ ከቆየ በኋላ በ1995 የወያኔ ባለሥልጣናት ፓርላማ ሳያቀርቡ የክልሉን መንግሥት ሳይነግሩ (‘ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ’) በሄሊኮፕተር መተማ አካባቢ ወርደው ቁጥር 3፣ 4፣ እና 5ን የሚባሉትን የእርሻ ቦታዎች ለሱዳን ፈርሞ እንዲያስረክብ የአካባቢውን አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ዓለም ገሌን አዘዙ። አገር ወዳዱም አሻፈረኝ በማለቱ ለአራት ኣመት እንዲታሰር ሆኗል። ከወያኔ ቀንደኛ መሪዎች አንዱ የሆነው አባይ ጸሃዬ ተደብቆ ፈረመላቸው። የተባለው ፊርማ ፓርላማ ያላወቀውና የአማራውም ክልል ያልተሳተፈበት በመሆኑ ውድቅ ነው።

ህ ወ ሃ ት ስልጣን ከጨበጠ በኋላ የሱዳኑ በሽርና የወያኔ ባለስልጣኖች በመቀሌ ከተማ ተደጋጋሚ ፓርቲ ማድረጋቸውን ከሩቅ ሆነን የታዘብነው ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ላይ ተደብቀው ሲመክሩ እንደኖሩ ግልጽ ነው። ስልጣን ከጨበጡ ጀምሮ ከሱዳን በኩል የወሰን መካለሉ ስራ እየተካሄድ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። የሴራቸውን ውጤት ከሱዳንና የአፍሪካ የዜና ምንጮች ማወቅ ችለናል። በየጊዜው በሚፈጠረው ግብግብ ብዙ ገበሬዎች ንብረታቸው ወድሟል፣ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የኢ ህ አ ደ ግ አመራር አባላት መሬት አልሰጠንም እያሉ ተገዘቱ። መለስ ሲጠየቅ አንድም የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን አልተሰጠም ብሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዋሸ። ሆኖም ከ1998 ዓ ም በኋላ በውጭ የዜና ምንጮች ስምምነት እንደተደረሰ አድርገው በመዘገባቸው በተለይም በ2001 ቮይስ ኦፍ አሜሪካ ( ቪ ኦ ኤ)፣ ናይሮቢ አዲስ አበባና ካርቱም በተደረገው ስምምነት ምክንያት የኢትዮጵያ ገበሬዎች መፈናቀላቸውንና መገደላቸውን በመዘገቡ፣ ጉዳዩ ወደፊት አፍጦ መጣ። በታህሳስ 2008 በኢትዮጵያ ድንበር ኮሚቴ አስተባባሪነት ብዛት ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሙያ ማህበራት በድብቅ የተደረገውን ስምምነት ተቃውመው ለተባበሩት መንግሥታት ጸሃፊ ደብዳቤ በመጻፋቸው እና የሕዝብ ፊርማ በማስገባታቸው ጠቅላይ ሚንስተር ሓይለማርያም ደሳለኝ መሬት አልሰጠንም ብሎ እንዲያስተባብል ተገደደ።

የአብይ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ባለፉት ሁለት የእርሻ ወቅቶች በአማራው ክልል የጸጥታ አካላትና በአካባቢው ሕዝብ መካከል በተፈጠረው ጥሩ መናበብ ገበሬው መሬቱን አስጠብቆ የኢትዮጵያ ገበሬዎች የእርሻ መሬታቸውን እንደገና ተቆጣጠሩ። ለሁለት ኣመት ካረሱት በኋላ ይህ አሁን የምናየው አዲስ ሁኔታ ተፈጠረ። ባለፈው አንድ ወር ጀምሮ ድንበራችን ጥሶ የገባው የሱዳን ጦር ሰራዊት መሬታችን እንደያዘ ይገኛል። ይህ አዲስ ህኔታ ካለፉት ሁሉ የተለየ ድፍረት የተሞላበት ነው። ሱዳኖች ሁለተኛ ክፍለ ጦራቸውን ያሰለፉ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በሁመራ አቅጣጫ ሉግዲ ውስጥ ጦር አስፍረዋል (ሕ ወ ሃ ት አመራሮች ምን እንዳሉ አናውቅም!)፣ የጓንግ ወንዝን (‘ሕዝቡ ወሰናችን የጓንግ ውንዝ ነው ይላሉ) ተሻግረው ከአብደራፊ እስከ መተማ ባለው ደለሎ/ጠረፍ ወርቅ/ሽመል ተራራ በሚባሉት ስፍራዎች አልፈው አልፈው ወታደሮቻቸውን አስፍረዋል። እንዲሁም ወሰኑን ታኮ በሚሄደው ከሺንፋ ወንዝ ደቡብ ነፍስ ገብያ በሚባለው ጦራቸውን አልፎ አልፎ አሰፍረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ጉዳዩን በቸልታ ያየው አይመስልም፣ ጠንከር ያለ ጦር ወደስፍራው አጓጉዟል። አሁንም በውስጣችን ያለው መናቆር፣ የህዳሴ ግድብና የአካባቢው ፖለቲካ በጉዳዩ ላይ ተጸእኖ ይኖረዋል ብለን እንገምታለን። የህ ወ ሃ ትን ሚናም አቃሎ ማየት ስህተት ነው። በዚህ ሁሉ መሃል መንግሥት የሕዝብን ሚና አሳንሶ እንዳይመለከት አደራችን የጸና ነው። ደርግ እንዳደረገው በመጀመሪያ የአካባቢውን ሕዝብ የሚለውን ማዳመጥ የግድ ነው።

በድንበር አካባቢ ያለው ሕዝብ ወሰኑን ሲያስከብር ኖሯል። በተለይ ጠረፍ ጠባቂ የሚባሉ አንቱ የተባሉ ቤተሰቦች ከልጅ ልጅ እየተወራረሰ የጥበቃውን ስራ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ከወያኔ መንግሥት በስተቀር ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መንግሥታት እንደ ነጭ ለባሽ ወታደር በመቁጠር የመሳሪያ እገዛ ያደርጉላቸው ነበር። ወሰኑን ከነታሪኩ ጥርት አድርገው ያውቁታል። መንግሥት እነሱን ሳይዝ ስለወሰኑ መነጋገር መደናበር ይሆናል። ሁኔታው በቆየው መቀጠል የለበትም። ሱዳን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ከያዘቻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ለቃ መውጣት አለባት። የኢትዮጵያ መንግሥት በተገኘው መንገድ ሁሉ ይህን ማስፈጸም ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። ባጠቃላይ ያለው ሁኔታ አገራዊ ጥሪ ማድረግን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። ለአገር አቀፍ ጉዳይ ቅድሚያን እሰጣለሁ የሚል ሁሉ የመደማመጥና በጥንቃቄ የመራመድ ግዴታ እንዳለበት ማሳሰብ እንወዳለን። ወደፊት ሁኔታው እንደፈቀደ በሁለቱ አገሮች ከሕዝብ ያልተደበቀ ዘላቂና ትውልድ ተሻጋሪ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል።

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኑር

የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት2 views
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin