Search
  • gyisma83

የ2012 ጥምቀት አከባበርና የሀዘን መግለጫ

ጥር 11 2012 ዓ ም

በጎንደር የጥምቀት በዓል ስለደረሰው ጉዳት የሐዘን መግለጫ!

የጥምቀት በዓል በአገራችን በኢትዮጵያ በየዓመቱ በከፍተኛ ድምቀት ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው። የ44ቱ ታቦታት መገኛና የነገስታት ልዩ አሻራ በሆነችው በጎንደር ከተማ ደግሞ ትኩረት ተሰጥቶት በየዓመቱ ድምቀቱ እየጨመረ የሚከበር በዓል በመሆኑ የብዙ ቱሪስቶችንና እንግዶችን ቀልብ በመሳብ እጅግ ብዙ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት ሃይማኖታዊ በዓል ነው። ጥምቀት የሃይማኖት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የባህልም ነው።

በተለይም በዚህ ዓመት፣ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ( the United Nations Educational, Scientific and Cultural Organization) የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በመወሰኑ ለበዓሉ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት እጅግ የላቀ ዝግጅት ተደርጎበታል። የኢትዯጵያ ፕሬዚዳንት የሆኑትን ክብርት ስሃለወርቅ ዘውዴ፣ ክብርት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፤ ከፍተኛ ባለስልጣናትና እንዲሁም ከተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች የተጋበዙ እንግዶችና ብዛት ያላቸው ቱሪስቶች ይህን ታላቅ በዓል ለመታደም ጎንደር ላይ ሲሰባሰቡ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ሆነን የተከታተልነው በደስታ ሲቃ ነበር።

በእርግጥ በቤተክርስቲያን፤ በሕዝቡ፤ በክልሉና በከተማው አስተዳደርና በጸጥታ አካላት ለበአሉ ዝግጅት የነበረው የተቀናጀ የቡድን ስራ በጣም አስደሳች እንደነበር በግልጽ የታየ ነበር። ስለሆነም ነው የበዓሉን ድባብ በሽብር ለማጨናገፍ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የተንቀሳቀሱ የተንኮል መልዕክተኞች ሊያዙ የቻሉት።

ሆኖም በዚህ ድባብ እያለን በ11/05/2012 ዓ/ም የጥምቀት በዓል ዕለት፣ የጥምቀት ስርዓቱ በሚከናወንበት ወቅት የበዓሉ ታዳሚዎች ባህረ ጥምቀቱን የተሻለ ቦታ ላይ ሆነው እንዲያዩ የተሰራው የዕንጨት ማማ በድንገት ተደርምሶ ያልታሰበ የሞትና የመቁሰል አደጋ በሰዎች ላይ በመድረሱ የሁላችንም ልብ በሃዘን ተሰብሯል። በጣም አዝነናል።

ከዚህ ክስተት የምንማረው ትልቅ ነገር፣ ይህ በዓል ወደ ጎንደር የሚስበው የሕዝብ ብዛት እያደገ የሚሄድና ከየክልሉ ብቻ ሳይሆን፣ ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊም ለዚህ በዓል በብዛት የሚተምበት መሆኑን ነው። ይህ ለጎንደር ሕዝብና አካባቢው ትልቅ የሶሺያልና የኢኮኖሚ ጥቅም እንደሚያስገኝለት እሙን ነው። ስለዚህ አሁን የደረሰው አደጋ ደግሞ እንዳይደርስ ቀድሞ ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል እንላለን። ለዚህም ቤተክርስቲያን መንግስትና ሕዝብ ሁላችንም በመተባበር፤ ለጥበቃ አመች የሆነ፣ ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ በዓሉን ሊያስተናግድ የሚያስችል በቂ ቦታ እንዲዘጋጅ እንዲደረግ ለማሳሰብ እንወዳለን። የጎንደር ህብረትም ተባባሪ በመሆን የተቻለውን ሁሉ በማድረግ እንደሚተባበር በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እንወዳለን።

በመቀጠልም በዚህ ደማቅ በዓል ላይ ይህ ያልታሰበ ድንገተኛ ክስተት ቢፈጠርም እንኳ በዓሉ በአማረ ሁኔታ እንዲያልፍ ከፍተኛ ርብርብ ላደረጉ የቤተክርስቲያኗ አመራርና ጠቅላላ ምዕመናን፤ ለክልሉና ለከተማው የአስተዳደርና የጸጥታ አስጠባቂና ደህንነት መ/ቤት፤ ለማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች፣ ለወጣቶችና አገር ወዳድ ለሆነው እንግዳ ተቀባይ ሕዝባችን በሙሉ አድናቆታችን ከፍ ያለ ነው። እንዲሁም በክብርት ፕሬዚዳንቷ የሚመራው ከፍተኛ ባለስልጣናት ልዑክ፤ ክብርት ቀዳማዊት እመቤት፤ ከጋሞ ለመጡ እንግዶች፤ ከተለያየ የዓለም ክፍል በበዓሉ ለተገኙ የውጭ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ ከኤርትራ በዓሉን ለማክበር የታደመውን ልዑክ፤ ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል ተጉዛችሁ በዓሉን ለአደመቃችሁ ኢትዮያውያን ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን።

በመጨረሻም በዓሉን በደስታ በማክበር ላይ እያሉ በድንገት በደረሰው አደጋ በሞት ለተለዩን ወገኖች እግዚአብሄር አምላክ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያስቀምጥ። ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ይስጥልን። ቆስለው በሕክምና ላይ ያሉትን ደግሞ ምህረቱንና ፈውሱን እንዲያድልልን ልባዊ ማኞታችን እንገልፃለን።

ለሚቀጥለው ዓመት የጥምቀት በዓል በደህና ያድርሰን።

የጎንደር ሕብረት።

1 view
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin