Search
  • Abebe Gelagay

በአማራና በቅማንት ማህበረሰቦች መካከል ስለተፈጠረው ሁኔታ ከጎሕ የተሰጠ መግለጫ


አገራችን ላለፉት 27 ዓመታት በመንግሥት በተተለመና በተመራ የተሳሳተ የጥፋት ፖሊሲ፣ ቅኝትና አካሄድ ጎዳና ቆይታ አዲስ የዲሞክራሲና የተስፋ ጎዳና ጉዞ በመጀመሯ ነፃነት የራበው ህዝብ እፎይታን አግኝቷል። ለዚህ አዲስ ሁኔታ ታጋዩ ህዝብና በመንግሥት ውስጥ የነበሩ የለውጡ ደጋፊዎች ያደረጉት ተደጋጋፊ ትግል ለተገኘው ለውጥ ምክንያት ናቸው። ሆኖም ለውጡ በጀመረው ጎዳና እንዲጓዝና አስተማማኝ እንዲሆን ገና ብዙ ትግልና ድካም እንደሚጠይቅ ላንድ አፍታም ቢሆን መረሳት የለበትም። አሁን በየአካባቢው ከመንደር እስከ ዩኒቨርስቲዎች የሚታየው ሕዝብና ሕዝብ ማጋጨት፣ ያልሆኑ ጥያቄዎችን እያነሱና አሉባልታዎችን እየነዙ ሁከት መፍጠር የሚያሳየው የለውጡን ለጋነትና በለውጡ የተከፉና የተገኘውን ለውጥ ለማጨናገፍ ሌት ተቀን የሚባትሉ እንዳሉ ነው። ከሁሉም በላይ በየአካባቢው መሣሪያ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ነፍስ በማጥፋት፣ በማፈናቀልና ንብረት በማውደም ብዙ ጉዳት እያደረሱ ነው። ከእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ አንዱ በምዕራብ ጎንደር የታየው የቅማንትና አማራ ማህበረሰቦችን ‘ልዩነት!’ ምክንያት ያደረገ እራሳቸውን በህዝብ ወኪልነት የሰየሙ ታጣቂዎች የሚካሄደው ድርጊት ነው።

ለውጡ ከመምጣቱ በፊት የቅማንት ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄን አስመልክቶ ስህተቶች ተፈጽመዋል። ደባዎችም ተሰርተዋል። በተለይም በእነዚያ ዓመታት የአማራ ክልልን በመዳፋቸው ስር አድርገው የወያኔን ተልእኮ ለማስፈፀም ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ በክልሉ ውስጥ የተሰገሰጉ ካድሬዎች በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ሊኖር የማይገባው ግጭት እንዲኖር አድርገዋል ብለን እናምናለን። ለደረሱት ጉዳቶች ሁሉ ተጠያቂም ናቸው።

እንደሚታወሰው በ2000 ዓ. ም. (እ አ አ) በተካሄደው የህዝብ ቆጠራ ወቅት ቅማንት የሚለውን አማራጭ በአማራጮች ዝርዝር ውስጥ አልተካተተም ነበር። ለምን?? ተራ ስህተት ነው ወይስ ደባ?

በቅማንት ‘ክልል’ ውስጥ ሊጠቃለሉ የሚገባቸው ቀበሌዎችን ቁጥር አስመልክቶ የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረቶች መውደምን ያስከተሉ ግጭቶች ደርሰዋል። የሁለቱ ማህበረሰቦች መካለል አጠያያቂ መሆኑ እየታወቀ መንግሥት 69 ቀበሌዎችን የሚያጠቃልል ክልል ቢፈቅድም እራሱን የቅማንት ማንነት ኮሚቴ ብሎ የሰየመው ቡድን የቀሩት 3ቱ ካልተጨመሩ በማለቱ ክልሉ ሊመሰረት እንዳልተቻለ ይታያል።

በጥቅምት 2008 ዓ. ም. (እ አ አ) በመተማ፣ ቋራ፣ ሸኽዲና ሺንፋ በተነሱ ግጭቶች ምክንያት የብዙ ዜጋዎች ህይወት አልፏል። በእነዚሁ ቦታዎች በጥቅምትና በህዳር 2011 ተመሳሳይ ጉዳቶች ደርሰዋል። ከሁለቱም ማህበረሰቦች ወገን ብዙ ሰዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል። የአማራም ሆነ የቅማንት ማህበረሰብን እንወክላለን ብለው መሳሪያ አንግበው፣ ኬላ አቁመው፣ የህዝቡን እንቅስቃሴ ሲገድቡና በክልሌ አታልፉም ወይንም ከክልሌ ውጡ ሲባባሉ መንግሥት ዝም ብሎ ማየት ምን ማለት ነው? የሁለቱን ማህበረሰቦች እውነተኛ ፍላጎት ለመረዳት በመጀመሪያ መንግሥት ጸጥታውን መጠበቅና ማረጋጋት ይጠበቅበታል። ይህ ከሆነ ነው እውነተኛ የህዝብ ወኪሎች ሊመረጡና በየማህበረ ሰባቸው ያለውን እውነተኛ ፍላጎት ማወቅ የሚቻለው። ይህ ከሆነ በኋላ ነው እውነተኛ የሁለቱ ማህበረሰቦች ወኪሎች በሁለቱ ማህበረስቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ላይ ገንቢ ውይይቶች ሊያካሄዱ የሚችሉት።

በጥቅምት ወር 2018 ዓ. ም. ይህን እሳቤ መሰረት በማድረግ ጎንደር ከተማ ውስጥ የሁለቱ ማህበረሰብ አባሎች የተገኙበት ስብሰባ ተካሂዶ ሁለቱ ማህበረሰቦች በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በቦታና በስነ ልቦና የተሳሰሩ፤ ተጋብተው፣ ተጎራብተው፣ ክርስትና ተናስተው ክፉውንና ደጉን ተካፍለው የኖሩ ማህበረሰቦች መሆናቸውን በመዘከር አሉ የሚባሉትን አለመግባባቶች በሽምግልና ለመጨረስ ስምምነት ላይ ተደረሰ። 20 የሽማግሌዎች ኮሚቴ አባላትን መርጦ 10ሩ ወደመተማ ፣የቀሩት 10ሩ ደግሞ ወደ ጭልጋ እንዲሄዱ ወሰነ። በስምምነቱ መሰረት ሽማግሌዎቹ ስምሪት ሲጀምሩ በዚህ የተደናገጡ ታጣቂዎች ግጭት አስነስተው ጥረቱ እንዲዘገይ ለማድረግ ችለዋል። ይህን ሂደት የተከታተለው የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ሁለቱ ማህበረሰቦች ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ለሽምግልናው ወጭ የሚውል የገንዘብ እርዳታ አድርጓል። በዚህ አጋጣሚ የክልሉ መንግሥት ይህን በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ለሚካሄደው የሽምግልና ጥረት ድጋፍ በመስጠቱ እናመሰግናለን። ሆኖም ለሂደቱ አስፈላጊ የሆነው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖሮ በማድረግ ላይ እጥረት ታይቶበታል እንላለን። እነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆ፣ ነፃ ውይይት እንዲያካሂዱና ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲፈቱ ከማንም ወገን ተፅዕኖ እንዳይደረግባቸው መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ሊያደርግ ይገባል። ሁለተኛ መንግሥት ሆነው፣ እራሳቸውን የህዝብ ወኪል አድርገው፣ እኛ ነን የምናውቅልህ ብለው በህዝቡ ላይ በዘመቱ የታጠቁ ሃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ መንግሥት ግዴታውን እንዲወጣም እንጠይቃለን። እንዲሁም የተፈናቀሉት ወደነበሩበት፣ ተማሪዎች ወደ ትምሀርት ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ እናሳስባለን። የክልሉ መንግሥት እንወክላለን ከሚሉ ካድሬዎች ጋር ሳይሆን ወደ ሕዝቡ ወርዶ ቀጥተኛ ውይይት በማካሄድ ብቻ ነው እውነተኛ መፍትሄ የሚያገኘው ብለን እናምናለን። በቤተሰብ መካከል ግጭት ያለ ነው። ሆኖም ይህን ለጥጦ፣ በባዕድ ሃይሎች ተታሎ፣ የነገውን ሳያዩ ወደ ጥፋት ጎዳና መጓዝ ሁላችንንም ያጠፋል። ስለሆነም በትእግስትና በአርቆ አስተዋይነት ችግሩን እንዲፈቱ ለሁለቱ ማህበረሰቦች ጥሪያችንን እናቀርባለን። እግዚአብሔር የተጎዱትን ሁሉ ያፅናናልን።

የወደፊት እጣችን አንድነታችን፤


208 views
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin