Search
  • Abebe Gelagay

ስለአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን ከጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ


የካቲት 11 2011 ዓ. ም.(2/18/2019)

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሺንን አስመልክቶ ከጎንደር ህብረት የተሰጠ መግለጫ

ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ በአገራችን የተገኘው ለውጥ የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት አየር እንዲተነፍስ ከማድረጉም በላይ ያለበትን የኢኮኖሚና የፍትህ እጦት በትልቅ፣ በጣም በትልቅ የተስፋ ምጋቤ እንዲጓዝ እያደረገው ነው። የዚህ ጉዞ መልካም ጎን እንዳለው ሁሉ መጥፎ ጎንም አለው። ህዝቡ ዘለዓለም የኖረ ችግር ባንዴ አወላልቆ መጣል እንደማይቻል ቢያውቀውም ፍትህ ይጠብቃል። ዳኛ ተሰይሞ ፍርድ ከተሰጠ የእስካሁን ፍትህ መጓደል እንዲቀጥል አይጠብቅም ። ፍትህነት የጎደለው፣ የጨነገፈ ፍርድ ብሎ ይታገለዋል። የታሪክ ጠባሳ ሆኖ ለትውልድ መተላለፉ የማይይቀር ነው። በዚህም አያበቃ፤ አንድ ትውልድ ያበላሸውን ፍርድ ሌላ ትውልድ ለማስተካከል የሚከፈለው የሰው ህይወትና የኢኮኖሚ ሃይል ድርብ ድርብርብ እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ግዴታ ነው።

በታሪካችን ውስጥ ዘርን መሰረት ያደረገ ድንበር መካለል ኖሮ አያውቅም። ንጉሶች፣ መስፍኖች ግዛታቸውን ለማስፋፋት በጦር፣ በጋብቻና አንዱን ደግፎ ሌላውን በመጣልና በማበር ሰፊ ግዛት ይዞ ለማስገበር ይዞታቸውን ለማስፋፋት መዋጋት በታሪካችን ውስጥ የነበረ ነው። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ግን በህወኅት መሪነት የዘር ወሰን ለማስፋት በየአካባቢው በቦታው የኖረውን ሕዝብ በማፈናቀልና የራስን ህዝብ ማስፈር፣ በሃይል ይዞታዎችን ማስፋት፣ ይህን ለማስፈፀም የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን መፈፀም ባጠቃላይ ሰብአዊ መብቶችን በፅኑ መጣስ በሰፊው ተመዝግበዋል።

በቅርቡ ከላይ የተነሱትን ችግሮች ለመፍታት በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ በፈለቀው ጽንሰ ሃሳብ ተመርኩዞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ የወጣውን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላትን ስም ዝርዝር ተመልከተናል። ለእርቀ ሰላም የተባሉትንም እንዲሁ አይተናል። የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄን አስመልክቶ ለተነሳው ችግር መፍትሄ እንዲሰጥ ኮሚሽን ይቋቋማል ሲባል በቀና መንፈስ አይተነው ነበር። ሆኖም አንዳንድ የታዘብናቸው ነገሮች አሉ። ገና ኮሚሽኑ ስራውን ሳይጀምር! አንድ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ግለሰብ የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ አስመልክቶ ውሳኔ መሰል ንግግር ሲያደርጉ ሰማን፤ የኮሚሽኑን አባላት ዝርዝር ስንመለከትም አንዳንድ መካተት የሌለባቸውን ስሞች በማየታችን ላለው ሁኔታ ፍትሃዊ ሽፋን ለመስጠት ነው ወይስ ለጉዳዩ ግዴለሽነት መኖር ብለን እንድንጠይቅ ተገደናል።

እነዚህ የኮሚሽን አባሎች የተመረጡበት መመዘኛ ምንድን ነው? መራጩስ ማነው? የህዝቡ ሚናስ የት ላይ ነው። የሚካለሉትስ እነማን ናቸው። በማን ተወክለው ነው? አንዳንድ ፍትህ በሰፈነባቸው አገሮች በዳኛነት የተሰየመን ወይንም ለሽምግልና የቀረበን ግለሰብ ባለ ጉዳዮቹ ገለልተኛ አይደለም ለዳኝነትም ሆነ ለሽምግልና እንዳይቀመጥብኝ ካሉ ያ ግለሰብ በዳኝነትም ሆነ በሽማግሌነት አይሰየምም። ድንበር ለማስፋት ጦር ያዘመቱ ሕገ መንግስት የቀረፁ ሕዝብና ሕዝብ ያፋጁ በአንድ ዘር ላይ ዘመቻ ያካሄዱ በዚህ ኮሚሽን ውስጥ ቦታ የላቸውም ብለን እናምናለን።

መንግሥትም ሆነ፣ ይህን ችግር እንፈታለን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በአንድ ወቅት ጉልበት ተሰምቷቸው በጦር አንድን ህዝብ አስለቅቀው የራሳችን የሚሉትን ህዝብ የሚያሰፍሩ በየትም አካባቢ ይሁኑ በየትም የሰሩትን ኢሰባዊ ተግባር በፍራቻም ሆነ በቸልተኝነት ማለፍ የለባቸውም። በታሪክ ተወቃሽ ከመሆንም በላይ ዛሬ ደካማ መስሎ የምታዩት ግፍ የተፈጸመበት ህዝብ ነገ ተጠናክሮ እንደሚመለስ አትጠራጠሩ። ግፍን ቅሚያንና ሰቆቃን ባጠቃላይ ኢሰባዊ ድርጊትን አውግዘን ለፍትህ ካልቆምን ለኢሰባዊ ድርጊት የይቀጥል ፍቃድ መስጠት ይሆናል።

ስለሆነም የሚመለከታቸው አካሎች መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ግልፅ በሆነና ከባለ ጉዳዩ ህዝብ አይን ባልራቀ ሁኔታ እንዲሰሩ እናሳስባለን። ይህን ስንል 1/ ለኮሚሽን አባልነት የሚያበቁ መመዘኛዎች (ገለልተኝነት፣ ታሪክ አዋቂነት፣ ሚዛናዊነት፣ የግለ ሰቡ ቅድመ ታሪክ፣ ስለ ጉዳዩ ያለው ግንዛቤ...ወዘተ) በቅድሚያ እንዲዘጋጅ፤ ለህዝቡም እንዲገለጥ። 2/ በመመዘኛዎች ላይ የተመሰረተ፣ ሁሉንም የህብረተ ሰብ ክፍሎች ያካተተና ሚዛኑን የጠበቀ ኮሚሽን እንዲቋቋም፤3/ ሁሉም ወገኖች ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ እድል እንዲሰጥ የጎንደር ህብረት ይጠይቃል። ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል የሚል ስጋታችንን ማካፈል እንወዳለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ


100 views
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin