Search
  • Abebe Gelagay

አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ


መስከረም 20 2012 ዓ. ም. (10/01/2019)

‘አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ’

የቅማንት ማንነት ጥያቄ በሚል በወያኔ ተጠንሰሶ፣ በአማራው ክልል ውስጥ በሰገሰጓቸው አቀንቃኞች ተላላኪነት በተለያየ መንገድ ማሕበረሰብን ከማሕበረ ሰብ ለመለያየት ሲገፋ የቆየው የክልል ጥያቄ ሴራ ሰሞኑን ደግሞ አገርሽቶ ወጥቷል። እራሱን የቅማንት ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው የታጠቀ ቡድን ሰሞኑን በፀጥታ ኃይሎች ላይ ተኩስ ከፍቶ ጉዳት ማድረሱንና ፀጥታው መደፍረሱን ከክልሉ መንግሥት እየሰማን ነው።

ይህን ችግር የቅማንት የማንነት ጥያቄ እያልን ከምንጠራው ይልቅ ‘ወያኔና ጠባብ ብሔርተኞች በአማራው ክልል ላይ ያወጁት ጦርነት’ ብለን ብንጠራው ለመፍትሄው ፍለጋ ሳይረዳ አይቀርም። ለምን የአማራና የቅማንት ግጭት እያልን እናወራለን? ሁለቱ ማሕበረሰቦች በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በታሪክ፣ በቦታና በስነልቦና አንድ የሆኑና ተጋብተው ተዋልደው በብዙ ክር የተሳሰሩና የተጋመዱ የማይለያዩ ሕዝቦች ናቸው። ይህን ሃቅ የአማራና የቅማንት ማሕበረሰቦች ለአንድ አፍታም ስተውት አያውቁም።

ችግሩ የተጠነሰሰውም ሆነ የተሸረበው በሕወሃትና አማራ ክልል ውስጥ በተሰገሰጉ የሕወሃት ወኪሎች ነበር። ሕዝብ እንካለል ብሎ ሳይጠይቅ ክልል ሰጥተናችኋል አሉ። ጽንፈኛ ቡድኖች የአገሩን ፀጥታ ሲያደፈርሱ የክልሉም መንግሥት ሆኑ የፌደራሉ መንግሥት እርምጃ ሳይወስዱ የመጠናከሪያ ጊዜ ሰጧቸው። ጸጥታውን መንግሥት እንዲያስከብር በሕዝብ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ባለመሰጠቱ በመተማ አካባቢ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ ጎንደር ከተማ ደረሰ። ይህ ሁኔታ ግድ ሆኖበት መንግሥት አንዳንድ እርምጃዎችን ከወሰደ በኋላ አንጻራዊ ፀጥታ ተገኝቶ ነበር። ሕዝቡም የተገኘውን ፋታ በመጠቀም በሽማግሌዎች የዘለቄታ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ ባለበት ወቅት የሰሞኑ ሁኔታ ተፈጠረ። ምንም እንኳ ሕዝቡ ሰላም ለማስፈን የራሱን ጥረት ቢቀጥልም፣ ክልሉ ግን ሊያደርግ የሚገባቸውን አካባቢውን ከታጠቁ ሃይሎች ማፅዳት፣ በምሕረት የሚገቡትን እድል መስጠት፣ ያመፁትን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ፣ የመንግሥቱን መዋቅር ማጠናከር፣ ሽማግሌዎችን መደገፍ፣ የተፈናቀሉትን ማስፈር፣ የተሰደዱትን መመለስ እና የመሳሰሉትን እርምጃዎች ባለመውሰዱ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል።

በጣም የሚያስገርመው የክልሉ ሹማምንት በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰጧቸው መግለጫዎች ናቸው። ፀጥታውን ስላደፈረሱት ታጣቂ ሃይሎች ሲገልጹ ቀላልና ከባድ መሳሪያዎችን የታጠቁና የሰለጠኑ እንደሆኑ ከጀርባ ድጋፍ እንዳላቸው ነው። በመሰረቱ ይህ የኅወሃት መሪዎች ስራ እንደሆነ እንኳን የአማራው ሕዝብ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል። የምን ድብብቆሽ ነው? የክልሉና የፌደራሉ መንግሥታት እርምጃ የመውሰድ ሃላፊነት አለባቸው። እነዚህ ሰዎች ባሕሪያቸው የታወቀ ነው። ነገ ከባእድ አገር ጋር ወግነው ሊወጉን እንደሚችሉ አንጠራጠርም። ከዚህ በፊትም ለብዙ ሺ ዓመታት አብረውት ከኖሩት ሕዝብ ይልቅ የጎረቤት አገር ሕዝብ ይቀርበናል ብለዋል። ብዙ ያልደረስንበት ሃሳቦች ይኖራቸዋል። እንዲህ አይነት እኩይ አመለካከቶች እኛ ማሰብ ያቅተን እንጅ እነሱ ከማሰብ አልፈው በስራ ሊተረጉሙት እንደሚችሉ መርሳት የለብንም።

የክልሉ መንግሥት አውቆም ይሁን ባለማወቅ እያድበሰበሰው ያለው ጉዳይ አለ። በመሰረቱ ይህ ግጭት የአማራና የቅማንት ማሕበረሰቦች ግጭት አይደለም። ወይንም የመካለል ጥያቄም አይደለም። ይህ የአማራውን ክልል በተለይም የጎንደርን ሕዝብ ለማዳከም በሚፈልጉ ኃይሎች የሚካሄድ ጦርነት ነው። በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂው ሕወሃት ነው። ሕወሃት የመስፋፋት ዓላማው ላይ ደንቃራ የሆነውን የጎንደርን ሕዝብ በሁሉም ገጹ እንዲደቅና እንዲጫጫ ይፈልጋል። በአጠቃላይ አማራውን ለማዳከም ይህን አካባቢ በቅድሚያ ማዳከም ቁልፍ አድርጎ ወስዶታል። ይህ ድርጅት ለሃያ ሰባት ዓመታት በዚህ ላይ ሲሰራ የቆየ፣ በአካባቢው መዋቅር የዘረጋና በገንዘብና በጦር እራሱን ሲያደራጅ የቆየ ነው። ይህ አክራሪ ብሔርተኛ ቡድን የሌሎች አክራሪ ቡድኖች ድጋፍ እንዳለውም ግልፅ ነው። እንዲህ ያለ ጠላት አስቀምጦ ክልሉ ለምን ይዘናጋል? በወቅቱ መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች ለምን አልወሰደም? የአገር ሽማግሌዎች መክረው ዘክረው በምህረት መግባት ለሚፈልጉት ምህረት ስጡልን፣ እምቢተኞችን እርምጃ ውሰዱና ጸጥታውን አስከብሩልን፤ ቅማንትና አማራ ጠብ የለውም ሲሉ፣ ክልሉ ለምን ፊቱን አዞረ?? ለምን እርማጃ ከመውሰድ ታቀበ?

ሁከቱ የጀመረበት የምእራብ ጎንደር አካባቢ ከሱዳን ጋር ባለው የድንበር ጉዳይ ምክንያት ውጥረት እንዳለበት ግልፅ ነው። ወያኔ በነአባይ ፀሃዬና በነበረከት አማካኝነት እዚህ ቦታ ላይም ሌላ ቦምብ ቀብሮ ነው የሄደው። ይህ አካባቢ አትኩሮት የሚጠይቅ ነው። ከክልሉ አልፎ በአገር ደረጃ ሊታይና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። የፌደራሉ መንግሥት ለምን ግልፅ አቋም የለውም? ለምን የክልሉን ጸጥታ ለማስከበር እርምጃ አልወሰደም??

ይህ ጉዳይ ‘በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ሆኖብናል።’ እየከነከነን ያለው በሰኔ አጋማሽ ላይ በክልሉ ውስጥ በደረሰው አስከፊ ሁኔታ ምክንያት ክልሉ ከገባበት ትልቅ ትርምስና አለመረጋጋት አለመውጣቱ ግልፅ ነው። የሁኔታው ድንገተኛነት፣ የድርጊቱ አፈጻጸም፣ የደረሰው ጉዳት፣ በክልሉ ውስጥ የተወው ጥርጣሬ፣ ክልሉና ፌደራሉ የወሰዷቸው አጠያያቂ እርምጃዎች ሕዝባችንን ትልቅ ጥርጣሬ ውስጥ ከተዋል። እስካሁን ድረስ በክልሉም ሆነ በፌደራሉ መንግሥት ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ ባለመታወቁ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ሊኖረው በሚገባ እምነት ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንደፈጠረ ግልፅ ነው። አሁን ደግሞ በጭልጋ አካባቢ የደረሰው ትርምስ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ የነበረውን የመነመነ እምነት ጨርሶ የሚያጠፋ ሆኖ አግኝተነዋል።

የጎንደር ሕብረት እስካሁን በተደጋጋሚ ሲሰጥ የቆየውን ማሳሰብያ ሁኔታው እስካልተቀየረ ድረስ መልሶ መላልሶ ያቀርበዋል።

1ኛ/ ሕዝቡ አበክሮ ያቀረበውን በቅማንትና በአማራ ማሕበረ ሰቦች መካከል ጠብ የለም የሚለውን እባሌ ክልሉ ቢያቅረውም ይዋጠው። የህዝቡ ፍላጎት ነውና። ድሮም ቢሆን የክልልን ጥያቄ አንግበው የመጡት እነበረከት እንጅ የቅማንት ሕዝብ አልነበረም። አሁንም፣ ያለሕዝባችን ፍላጎት ጠላት የሰነቀረውን ክልል የተባለ የመለያያና የእልቂት ሴራ ፈርሶ፣ ሕዝባችን እንደ ሁልጊዜው በሰላም አብሮ የመኖር ጥያቄው እንዲመለስ እናሳስባለን።

2ኛ/ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ምሁራን በሁለቱ ማሕበረ ሰቦች መካከል ጠብ የለም፤ ምህረት ተሰጥቷቸው መግባት የፈለጉ ገብተው ሰላማዊ ሕይወት ይኑሩ፤ ባመፁ ላይ ደግሞ መንግሥት እርምጃ ወስዶ ፀጥታውን ያስከብር፤ እራሳቸውን ማቋቋም ለሚፈልጉ እርዳታ ይደረግላቸው ሲሉ ያቀረቡት ማሳሰቢያ ተፈጻሚ ይሁን። መንግሥትም መንግሥት ይሁን። አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዶ ሁለት እርምጃ ወደኋላ አይመለስ።

3ኛ/ በጎንደር ሕዝብ ጀርባ ላይ የታዘሉ ልዩ ልዩ ሃይሎች እንቅስቃሴ ላይ የክልሉም ሆኑ የፌደራሉ መንግስት እርምጃ ይውሰዱ። በአማራው ክልል ውስጥ በጥርጣሬ አግበስብሰው ሲያስሩ ምነው ፀጥታውን ያደፈረሱ፣ የገደሉና ሸፍተው የከተሙን ሃይ የሚል ጠፋ!?

የጎንደር ሕዝብ አንድነቱን በውድም ሆነ በግድ ያስከብራል፤

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር፤


44 views
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin