Search
  • Abebe Gelagay

መንግሥት መንግሥት መሆን ሲያቅተው!


የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ፣ የሕዝብን ደህንነትና ፀጥታ ማስጠበቅ፣ ሕግና ስነስርአት ማስከበር እና ፍትህ እንዲሰፍን ማድረግ ነው። እነዚህን ለመተግበር የመንግሥት አውታሮች አመች ሆነው መዋቀር ይገባቸዋል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የአገሪቱ አመራር አካሎች፣ የፖሊስ ኃይሉንና ፍርድ ቤቶቹን ጨምሮ የግለሰብን መብትና የሕዝብን ጸጥታ ለማስከበር እንደ አንድ አካል እየተናበቡ የሚሰሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ያልቻለ መንግሥት እንዳለ ሊቆጠር አይችልም፡፡ ዜጎች ለደህንነታቸው ዋስትና ካጡና ሰላማቸው ከተናጋ በምክንያትም ሆነ ያለምክንያት ህግ ከማክበር ይልቅ ወደ ሥርአተ አልበኝነት ያመራሉ፡፡ በባህላችን ‘በሕግ አምላክ’ የሚባለው ያለምክንያት አይደለም። ሕዝባችን በሕግና በፍትህ የሚያምን በመሆኑ ነው። አሁን ግን መንግሥት ሕግ ለማስከበር ያለው ቁርጠኝነት በመዳከሙ ምክንያት ይህ ባህላዊ ዕሴታችን እየደበዘዘ ነው፡፡

በዚህ መግለጫችን ስለ ፀጥታ፣ ሕግና ስነስርዓት፣ ፍትህ እና ሰላም ለማንሳት የተገደድነው ባለፉት ወራት በአማራው ክልል የደረሱትን አንዳንድ ፀጥታን ያደፈረሱ፣ ሰላምን የነሱ እና ስርአት አልበኝነትን ያነገሱ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው የተሰማንን ስጋት ለማንሳትና የሚመለከተውን ሁሉ በቸልተኝነት የሚታለፍ ጉዳይ እንዳልሆነ ለማሳሰብ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በምእራብና በመሃል ጎንደር ፀጥታ ደፍርሷል፤ ሰላም ተናግቷል፡፡ ብዙ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል። መሳሪያ ያነገቡ ሰዎች በግለሰብም ይሁን በቡድን፣ ከየትኛውም ቡድን ይሁኑ፣ በቀንም ሆነ በሌሊት ሰው እየገደሉ፣ ንብረት እየዘረፉ፣ ቤት እያቃጠሉ፣ ኬላ ሰርተው መኪና አስቁመው ለንግድ የሚንቀሳቀስ ዜጋን እየገደሉና እየዘረፉ ይገኛሉ። መንግሥትም እንደ መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ማዳንም ሆነ ንብረታቸውን መጠበቅ አልቻለም፡፡ ይህ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀዝቀዝ ፈንታ እየሰፋ አዲስ አካባቢዎችን እየጨመረ ሲሄድ እያየንው ነው። ከመተማ ተነስቶ ጎንደር ከተማ ገብቷል። ይህ የመንግሥት አለመኖርን ካላሳየ ሌላ ምን ያሳያል?

ደግመን ደጋግመን በመግለጫዎቻችንም ሆነ ለክልሉ መንግሥት በፃፍናቸው ደብዳቤዎች ያሳሰብናቸውን መልእክቶች አሁንም እናነሳለን። ይህ ከቅማንት ማንነት ጋር በተያያዘ የመጣው ችግር፣ ስር መሰረት ያለው ነው። ከ30 ዓመታት በፊት በህወሓት ተጠንስሶ በአማራው ክልል መንግሥት ውስጥ በሰገሰጓቸው ካድሬዎቻቸው ያላንዳች ተቃውሞ ሲገፋ የመጣ ነው። ከ 30 አመታት በፊት ጀምሮ ይህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በህ ወ ሓ ት ሰዎችና በካድሬዎቻቸው ቀርቦ ህዝብ ተቃውሞ መልሶታል። እቅድ ያለው ወያኔ ግን በየጊዜው ጥያቄውን እያስነሳ ጎንደርን በሁሉ ረድፍ በማዳከም የመስፋፋት ዓላማውን እውን ለማድረግ ከመጣር አቁሞ አያውቅም። ‘ወልቃይት ጠገዴ ሲሉን መሃል ጎንደር ላይ እርስ በእርሳቸው እናባላችዋለን’ በሚል ስሌት በመንግስት መዋቅሮች በኩል ብቻ ሳይሆን ሰርጎ ገቦችን አሰልጥኖ በመላክም ሰላም እየነሳን ነው። ለክልሉ አንድ የአባቶች አባባል አለን ‘ለሰለባ የመጣን፣ ነጠላ ቢጥሉለት አይመለሰም”።

የቅማንት የተለየ አስተዳደርን በተመለከተ፣ ጥያቄው ሁለቱ ማሕበረሰቦች የሚሳተፉበት ሂደት መኖር አለበት ብለን እናምናለን። የትኛው ማሕበረ ሰብ ነው ተሰብስቦ የሚወክለውን ኮሚቴ የመረጠው የቅማንት ነው ወይስ የአማራ? እስኪ ንገሩን መቸ ነው የቅማንት ህዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፅ የሰጠው? ደግሞ መካለልስ ቢኖር ተካላዮቹ ሁለቱም ወገኖች መኖር የለባቸውም? የክልሉ መንግሥት ሰዎች ሲሉ ሰማን እንጅ እኛ እስከምናውቀው እነዚህ ማህበረ ሰቦች ድንበር ኖሯቸው አያውቁም። የሁለቱ ማህበረስብ ወኪሎች እንኳ ቢቀርቡ ማካለል መቻላቸውን እንጠራጠራለን። ማን እምን ላይ ድንበር ይኸ ነው ብሎ ያካልላል! እዚህ ላይ የወያኔን ሰዎች ብቻ አይደለም የምንወቅሰው፤ ሃላፊነታቸውን ረስተው በቸልተኝነት የተመለከቱትን በአማራው ክልል ውስጥ የተሰገሰጉትን ባለሥልጣናት ጭምር ነው። ወደዚህ አስከፊ ደረጃ ያደረሱን ሁሉ ይጠየቁበታል።

የአማራ የክልል መንግሥት የችግሩን መጠንና የሚያስከትለውን ጣጣ ተረድቷል ብለን ማመን ያስቸግረናል። ይህ መንግሥት እኮ ከድንበር የተነሳ (መተማ) ችግር መሃል ከተማ (ጎንደር) እስኪገባ ድረስ እጁን አጣጥፎ ያየ ነው። እንዴት እንመነው! አንድም የችሎታ ችግር አለ፤ አለዚያም በመንግሥቱ ውስጥ ለሶስተኛ ቡድን የሚሰሩ አሉ። በአሁኑ ወቅት ይህ የክልል መንግሥት በጎንደር ክፍለ ሀገር ውስጥ ለውድድር ቢቀርብ የሚያሸንፍ አይሆንም። ኢህደግም ሆኑ አዴፓ ይህን በጥሞና እንዲረዱት አበክረን እናሳስባቸዋለን።

የፌደራል መንግሥቱም ቢሆን ችግሩ በቀጥታ ይመለከተዋል። በአገር ደረጃም ተመሳሳይ ችግሮች በየክልሉ አሉ። እነዚህ ችግሮች ለብዙ ዜጎች መሞት መፈናቀል እና ንብረት መውደም ምክንያት ሆነዋል። በአንድ ቦታ መንግሥት ድክመት ካሳየ በሌሎች ቦታዎች ተመሳሳይ ችግሮችን ሊወልድ፣ ያሉት ደግሞ ገዝፈው እንዲወጡ እድል ሊሰጥ እንደሚችል ማወቅ አለበት። ችግሮች ሂደታቸውን ጨርሰው እራሳቸውን በራሳቸው መፍትሄ ይሰጣሉ የሚለው ስሌት አያስኬድም። ባወጣ ያውጣው ካልሆነ በስተቀር።

አዎ! ከክልሉ መንግሥት ጋር ያለን ችግር በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደለም። በሰኔ ወር ውስጥ በክልሉ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ የደረሰው አስከፊ ሁኔታም አሳሳቢ ነው። ከዚህ በፊት ለክልሉና ለፌደራሉ መንግሥታት በፃፍናቸው ደብዳቤዎች እንዳስገነዘብነው የሁኔታው አስከፊነት፣ ድንገተኛነቱና የቀውስ ሰለባ የሆኑት ግለሰቦች ክልሉን ቀውስ ውስጥ መክተታቸው እንዳሳሳበን ገልጸናል። ችግሩን ለመፍታት የተወሰዱት አጠያያቂ እርምጃዎች፣ በክልሉም ሆነ በፌደራሉ መንግሥታት የቀውሱን መነሻ ምክንያት አለመግለፅ፣ ለዚህ በሃላፊነት የሚጠየቁ ሰዎችንም ለፍርድ ለማቅረብ አለመቻል፤ ይባስ ብሎ የጅምላ እስራቶችን ማካሄድ የአማራው ክልል ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ በክልሉና በፌደራሉ መንግሥታት ላይ ትልቅ ጥያቄ እንዲያነሳ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት በመንግሥት ላይ ትልቅ ጥርጣሬ አድሮበታል። በቀውሱ ሰለባ የሆኑት ቤተሰቦች የፍትህ ያለህ እያሉ እየጮሁ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በምርመራው ሂደት ላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ተጽእኖ በማድረግ የፖለቲካ ማወራረጃ እንዳያደርጉት ከፍተኛ ስጋት አለን፡፡ ይህን ችግር ለማርገብ አገር በቀልም ሆኑ ኣለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ሂደቱን በታዛቢነት እንዲከታተሉ ማድረግ ለአስተማማኝነቱ ትልቅ ድጋፍ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት(በተለይም የአማራው ክልል መንግሥት) ይህን ችግር በሚገባ ካልያዙት አሉባልታና ውንዥብር እንደሚያስከትልና ይህም ሁኔታ ወደ ሌላ ቀውስ ሊወስድ እንደሚችል መረዳት አለባቸው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በፊት ለክልሉ አመራር ያሳሰብነውን አሁንም እንደግማለን።

“ምንም እንኳ በክልልና በፌደራል ደረጃ የተጀመሩት የምርመራ ሂደቶች እንዳሉ ብንገነዘብም፣ በጎንደር ሕብረት እምነት ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች የሚፈቱት ገለልተኛና ፍትኃዊ የሆኑ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የጥቃቱ ሰለባ ወኪል እማኞች የተካተቱበት፣ ከማንም ተፅእኖ ነፃ የሆነ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሁኔታውን በጥሞና ሲመለከተውና ሲመረምረው ብቻ ነው። የዚህ ኮሚሽን የምርመራ ውጤት ለህዝብ ይፋ ሆኖ፣ ሕጋዊ ሂደትን ተከትሎ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲያገኝ ብቻ ነው ችግሩ መፍትሄ አገኘ ለማለት የሚቻለው። ይህ ሲሆን ሕዝባችን በፍትሃዊነት ላይ ሙሉ እምነት ይኖረዋል። የሆነው አሳዛኝ ክስተት ከግምትና ከአሉባልታ ነፃ ሆኖ ሕዝባችንም ለክልላዊና አገራዊ እድገትና አንድነት ጠንክሮ በጋራ እንዲቆም አወንታዊ ሚና ይኖረዋል የሚል ጽኑ እምነት አለን።”

የክልሉ መንግሥት በእሱና በሚያስተዳድረው ሕዝብ መካከል የተፈጠረውን ያለመተማመን ክፍተት፤ ሕዝቡን ባሳተፈ መልክ ችግሮችን በመፍታት የመተማመኛ ድልድይ እንዲገነባ አጥብቀን እንጠይቃለን።

ኢትዮጵያ ተከብራና ታፍራ ለዘለዓለም ትኑር!

የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት፤


10 views
  • s-facebook
  • Twitter Metallic
  • s-linkedin