top of page

ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በእርጥቡ

ኅዳር 26 ቀን 2013 ዓ. ም.(11/18/2020)






በሰሞኑ በጎንደር ዞኖች የትኅነግን ወረራ ለመቋቋም ከሚካሄደው ጦርነት ሌላ የጎንደር ህዝብ ሌላ ግንባር ከፍቶ በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰግስገው ሲያደሙት የቆዩትንና ሰላም የነሱትን ልዩ ረድፈኞች እየተዋጋ ነው። እንደሚታወሰው ወያኔ በ30 ዓመት ታሪኩ ውስጥ ህዝብና ህዝብን ማጋጨት፣ በህዝቦች መካከል እልቂቶች እንዲካሄዱ፣ ህዝብ እንዲፈናቀል፣ ንብረቶች እንዲወድሙ ማድረግ፣ ብሎም የሕዝቦችን አንድነት ንዶ ኢትዮጵያን ማፍረስ ደከመኝ ታከተኝ ሳይል ሲባዝንበት የቆየ እንደሆነ የታወቀ ነው። በጎንደር ሕዝብ ላይ ክከፈታቸው የማጥቃት ግንባር ውስጥ አንዱ የአማራና የቅማንት ማሕበረሰሰቦችን ማጋጨት ነበር። በአሁን ወቅት ይህን ሴራ ለማክሸፍ በላይ አርማጭሆና በታች አርማጭሆ ያሉ ወገኖቻችን በአካባቢው ህዝብ በተለይም በጎንደር ዙሪያ፣ በወልቃይትና ጠገዴ ሕዝብ እየተደገፉ ሁለቱን ማሕበረሰቦች ለማለያየት የተሴረውን ሴራ በማክሰም ላይ ይገኛሉ። ከወያኔ ጋር በመካሄድ ላይ ካለው ጦርነት ሌላ በመካከሉ እየተሽሎክኮሎኩ ሰላም የነሱትን ለማጥቃት ሕዝባችን ተጨማሪ ግንባር ከፍቷል።


በትኅነግ ያልተቋረጠ እኩይ ጥረት፣ በአማራው ክልል የተሳሳተ የጉዳዩ አያያዝ፣ በተከታታይ የፌደራሉና የክልሉ ባለስልጣናት ያሳዩት ቸልተኝነት ለብዙ ግጭት፣ መፈናቀሎችና የንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል። ሳይመረጡ እንወክልሃለን ባሉ የአሸባሪው የትህነግ ቅጥረኛ ድርጅቶች በተለይም እራሱን የቅማንት ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው የቅጥረኞች ጥርቅም ከመተማ እስከ ጎንደር ዙርያ በመሽሎክሎክ በሕዝባችን ላይ ያደረሰው ጥፋት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። እየተሹሎከሎኩ በመግደል፣ በማፈናቀል፣ ንብረት በማውደም፣ አፍኖ/አግቶ አፈላማ በመጠየቅ፣ የሕዝባችንን ሰላም፣ አንድነትና ወንድማማችነት ለመናድ ያላደረገው የለም። ይህ ድርጅት አልፎ ተርፎ የአሸባሪውና ጸረ ኢትዮጵያ ከሆነው ወያኔ ጋር በማበር ከባእድ አገራት ጋር ወግኖ ኢትዮጵያን በመውጋት ላይ ነው። አሁንም እንደትናትናው ሕዝባችን በራሱ አነሳሽነት በቃ ብሎ ተነስቷል።

እየተሹለኮሎኩ ሰላም የነሱትን፣ አፋኞች፣ የሕዝብ ንብረት ዘራፊዎችን አሸባሪዎችና ተላላኪዎችን ለመታገል፣ ባለፉት ጥቂት ወራት በላይ አርማጭሆና በታች አርማጭሆ በህዝቡና በአስተዳደሩ ትብብር ተደጋጋሚ ታላላቅ የሕዝብ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። በሁኔታው አብሮ የተሰቃየው የወልቃይት፣ የጠገዴና የጎንደር ሕዝብ አብሮነቱን በመግለጽ ድጋፉን ሰጥቷል። በጠቅላላ የጎንደር ክፍለ ሃገር ሕዝብ ሰላም አጥቶ የጦርነት አውድማ ሆኖ ከልማት ተገልሎ በመቆየቱ ተከታታይ ስብሰባዎች ከትክል ደንጋይ ሌላ በጭልጋና በጎንደር ተካሂደዋል። ሕዝቡ የራሱን የስራ ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቆ መንግሥት የሕግ ማስከበር ሚናውን እንዲወጣና በልማት ወደኋላ የቀረውን የጎንደር ክፍለ ሃገር ትኩረት እንዲሰጥ ለክልሉ መንግሥትና ለፌደራል መንግሥት ጥያቄውን በማቅረብ ላይ ነው።

በአሸባሪነት ከተወገዘውና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ወግኖ ከሚወጋን ትኅነግ ጋር ወግኖ በኢትዮጵያ ላይ የዘመተ ድርጅት ሁሉ አሸባሪ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ጠላት ነው። እራሱን በድፍረት የቅማንት ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ነው። በተለይም የቅማንት ማሕበረሰብና የአማራው ማሕበረሰብ የዚህ ድርጅት ቀጥተኛ ተጠቂዎች በመሆናቸው በአንድነት ተነስተው እየተፋለሙ ናቸው። የክልሉ መንግሥትና የፌደራሉ መንግሥት ይህን ድርጅት በሽብርተኛነት ሊፈርጀው ይገባል። ሰላም ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ጥብቅ እርምጃ በዚህ ቡድን ላይ መውሰድ ለነገ የማይባል ነው። ጎንደር የልማት ስራዎችን ማካሄድ የምትችልበት ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሮ እንሰሌሎቹ አካባቢዎች ስለኢንደስትሪያል ፓርክ የምታወራበት ጊዜ ቅርብ ነው ብለን ተስፋ እናደርጋለን። መንግሥት እንደ መንግሥት ፣ የክልሉም ሆነ የፌደራሉ የረሷትን ጎንደር ሰላሟን አስከብረው ወደኋላ ከቀረችበት የልማት ጎዳና ውስጥ ሊያስገቧት ይገባል እንላለን።

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!

Featured Posts
Recent Posts
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Classic
  • Twitter Classic
  • Google Classic
bottom of page