በድምጻዊው/ታጋዩ መሞት
ሰኔ 24 2012 ዓ ም (7/1/2020)
ለአርቲስት አጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰቦች ወዳጆችና የሀዘናችን ተካፋይ ለሆኑ ሁሉ፤
በአዲስ አበባ ከተማ በድምፃዊነቱ ብቻ ሳይሆን በታጋይነቱ የምናውቀው ታጋዩ አጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈፀመው የግድያ ወንጀል በጣም አሳዝኖናል። አጫሉ በአገር አቀፉ ትግል በተለይም የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄዎች መድረክ ይዞ በመውጣት ያደረገውን አስተዋጽኦ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ይህን ወጣት አርቲስት በለጋ እድሜው ለመቅጠፍ ያሴሩት፣ የጎዱት አጫሉንና ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነው። ይህ ሴራ ሕዝብና ሕዝብን፣ ብሔርና ብሔርን በማጋጨት አገሪቷን ብጥብጥ ውስጥ ለመክተት ባቀዱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ወንጀል ነው።
ይህ ጉዳት፣ ይህ ሀዘን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀዘን ነው። አገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ እንዲህ አይነት ብጥብጥ የሚፈጥሩ ግለሰቦች ይሁኑ፣ ቡድኖች ወይንም የፖለቲካ ድርጅቶች ለብዙ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆኑ ብቻ አይደለም የአገር ማፍረስ ተግባር ላይም የተሰማሩ እኩዮች ናቸው። ተደጋግሞ እንደታየው መንግሥት እንዲህ ዓይነት ወንጀለኞችን ይዞ ለፍርድ ባለማቅረቡና ባለመቅጣቱ ብዙ አገር ወዳዶችን እያጣን ነው። አሁንም መንግሥት ባስቸኳይ ወንጀለኞችን ይዞ ገለልተኛ በሆነ አካል ምርመራው እንዲካሄድና ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦችም የምናሳስበው እንዲህ አንዳንድ ወንጀለኞች በስሜታችን በመጫወት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር፣ ብሔርን ከብሔር ጋር በማጋጨት ሕይወት ለማጥፋት ንብረት ለማውደም ብሎም አገራችንን ወደ ማያባራ ብጥብጥ ለመክተት ለሚያደርጉት ሴራ ሰለባ እንዳንሆን ጥንቃቄ በተሞላበት፣ ሚዛን በጠበቀና ማስተዋልን በተላበሰ ፍትህ እንድንጠይቅ አበክረን እናሳስባለን። በዚሁ ሳብያ ሕይወታቸውን ላጡና ንብረታቸው ለወደመ ሁሉ ሃዘናችንና ድጋፋችንን እንገልጻለን።
ከዚህ ኣለም በሞት የተለየንን አርቲስት አጫሉ ሁንዴሳን ዘለዓለማዊ ሕይወት ያውርስልን።
ቤተሰቡን ያጽናናልን።
የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት፤