top of page

በጥቁር ገቢያ የውጭ ምንዛሬ...

በጥቁር ገበያው የውጭ ምንዛሬን መሸመት አገራችንን ይጎዳታልና እባካችሁ አገር ወዳዶች ይህን ልምድ አቁሙ።

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ትዝ የሚለኝ አንድ ተረት አለ። “ምነው እናቴ እንቁላል ስሰርቅ በቀጣሽኝ” የሚል። ህወሓት በአገራችን ሕዝብ ላይ ካስፋፋቸው ደዌዎች ወይንም በሽታዎች መካከል አንዱ ሌብነት ነው። ሰርቆ መዋሸት ልምድ ሆኖ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ፤ ያለ ስርቆት በስተቀር ኑሮን ለማሻሻል አይቻልም የሚል መጥፎ እሴት ተላምዷል። እኛስ የዚህ ሰለባ ሆነናል?

መወገድ ያለበት የሌብነት ባህል ለአገራችን ከፍተኛ ጉዳት አምጥቷል። ሰርቶና አምርቶ መብላት ነውር ሆኖ፤ ሌብነት እንደ ተራ ነገር ስር ሰዷል። ሌብነት ተቋማዊ ሲሆን ደግሞ ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ ለደህንነት፤ ለሕግ የበላይነት መሰናክል ነው። የውጭ ጠላቶች ዘዴውን ተጠቅመው የውክልና ጦርነት የሚካሂዱበት ወንፊት ይሆናል። ከህግ ውጭ የሚታየው ብዙ መሳሪያ በምንና በማን እየተሸመተ ነው?

ኢትዮጵያ ሃገራችን በራሷ ሕዝብ፤ በራሷ መዋእለንዋይ ፈሰስ፤ በራሷ ንበረትና ጥረት መመካት እንዳለባት ህወሓት በጀመረው ግጭትና አላስፈላጊ ጦርነት በገሃድ እያየን ነው። ሰሞኑን ፈረንጆች ለምን የኢትዮጵያን አቋም አያስተጋቡም? ለምን የህወሓትን፤ የጽንፈኞችን፤ የአመጸኞችን፤ የሽብርተኞችን ትርክት ያስተጋባሉ? እያልን እንጠይቃለን። ጥያቄው አግባብ አለው። መልሱ ግን፤ እኔ እስካማውቀው ድረስ ፈረንጆች ከራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም ውጭ የጥቁር አፍሪካዊያንን መብትና ጥቅም አስተጋብተው አያውቁም።

ለምሳሌ፤ ትላንት በአሜሪካ ኮንግሬስ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የኢትዮጵያን ፌደራል መንግሥት የሚወክል አልተጋበዘም። የተጋበዙት በተቆርቋሪነት ስም ተቃዋሚዎች ናቸው፤ በአብዛኛው ፈረንጆች። ብዙ ፈረንጅዎች ለኢትዮጵያ ደንታ የላቸውም። የፈረንጅ ወያኔዎች ብዙ ናቸው። ኸርማን ኮህን ለወያኔው አድልቶ የሚሰራው ለምንድን ነው? ምክንያቱም፤ አንድ ለንደን የሚኖር የስለላ ባለሞያ እንደተናገረው፤ የኢትዮጵያው ጠላት ኮህን በያመቱ $200,000 ዶላር ይከፈለዋል። ህወሓት ይህን ፈሰስ ለማድረግ ገንዘቡን ከየት አገኘው? ብለን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። ያገኘው ከኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ነው።

ይህ ትንተና አንድ አላማ አለው። ይኼውም፤ እኛ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አገራችንን እናፈቅራለን፤ ሕዝባችንን እናከብራለን፤ እድገቱን እንፈልጋለን ካልን ከዛሬ ጀምሮ ወደ አገር ቤት የምንልከውን ገንዘብና ከአገር ቤት ወደ ውጭ የሚላከውን ገንዘብ መሸመት ያለብን በጥቁር ገበያ መሆኑን ማቆም አለብን (We need to cease exchanging monies through the Black Market)::

ይህን አትኩሬ በመረጃ ላቅርብ። ዓለም ባንክ በነበርኩት ወቅት፤ ስለ እትዮጱያ ሃዋላ (Remittances from Ethiopia) አየሁ። በሕግ የሚገባው በዓመት $650 ሚሊየን የሚል። ትክክል አይመስለኝም በሚል ተከራከርኩ፤ ሰሚ አላገኘሁም። ከብዙ ዓመታት በኋላ ይህ የዓለም ባንክ ዘገባ አልተቅየረም። በ2017 የጥቁር አፍሪካ አገሮች $41 ቢሊየን እንዳገኙ ፒው የተባለው ድርጅት አስታውቋል። ከዚህ ናይጀርያ $22 ቢሊየን፤ ጋና $4 ቢሊየን፤ ኬንያ $1.6 ቢሊየን እንዳገኙ ዘግቧል። የኬንያ ዲያስፖራ ሶስት ሚሊየን፤ የኢትዮጵያ ደግሞ ሁለት ሚሊየን ነው ይላል። የኢትዮጵያ በሕግ የተመዘገበው ድርሻዋ (በሕግ የገባው) ግን $816,000,000 ነው። የኬንያን ግማሽ። ያስደነገጠኝና ያስቆጣኝ ግን ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ በሕገወጥ መንገድ የተላከውን ስመለከት ነው።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ

የጥቁር ገበያው የገንዘብ ምንዛሬ ባህልና ልምድ ለኢትዮጵያ ኪስራ ነው።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያዳከሙት “የቀን ጅቦች” ብቻ አይደሉም። እነዚህን አጥፊዎች በሚመለከት የፈጸሙትን ግፍ፤ በደል፤ጭካኔ፤ ከሃዲነት ወዘተ ለመግለጽ ቃላት ለማግኘት አልችልም። ዝርፊያውን በሚመለከት የጻፍኩትን መጽሃፍ፤ ማለትም፤ “ድርጅታዊ ምዝበራን” ከአማዞን አዛችሁ ልታነቡ ትችላላችሁ። የነሱ በሽታ ባህል ግን ስር ሰዷል።

ብናውቀውም፤ ባናውቀውም፤ ብንቀበለውም ባንቀበለውም፤ እኛም የችግሩ አካል ሆነናል። ምሳሌዎችንና ልናደርጋቸው የሚገባንን ተግባራት ከማሳሰቤ በፊት፤ ከሕግ ውጭ የውጭ ምንዛሬን ማካሂድ ጉዳቱ ምንድን ነው? የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ላቅርብ።

ከሕግ ውጭ የውጭ ምንዛሬ ገበያን መጠቀም በብዙ አገሮች የተለመደ ነው። ይህ ሕገወጥ ንግድ በተካሄደባቸው አገሮች፤ ለምሳሌ በዝምባብዊና በቬኔዙዌየላ ንግዱ የዋጋ ግሽፈቶችን አስከትሏል። አንዱ ብሄራዊ አሉታዊ ውጤት ይኼው ነው። አንድ ብር የሚያወጣ እቃ ሁለት ብር ወዘተ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። ማን ተጎዳ? የሚለውን ብንጠይቅ፤ ሸማቹ ይሆናል። የጥቁር ገበያው እየሰፋ ሲሄድ በሕግ የሚንቀሳቀሰው ክፍል ጫጩት እየሆነ ይሄዳል ማለት ነው።

አንድ ከ1947 እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ አንድ መቶ ልዩ ልዩ የአገር ገንዘቦችን (currencies) ሸፍኖ የተደረገ ጥናት ያሳየውን የጥቁር ገበያ ስዕል ስመለከት በአንዳንድ አገሮች የጥቁሩ ገበያ አሉታዊ ውጤት ያስከተላቸው የአመራር ውሳኔዎች አሉ። አንዱ፤ የጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠርና ገበያውን ለማስተካከል ሲባል ማእከካዊ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር ማድረጋቸው ነው። ይህም ሆኖ፤ ችግሩን ለመቆጣጠር ያልቻሉ አገሮች አሉ።

ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የገንዘብ ንግድ ሲካሄድ ችግር ከደረሰባቸው አገሮች መካከል አንዷ ዝምባብዌ ናት። አንድ ሰሞን፤ የዝምባብዌ ገንዘብ ዋጋ እጅግ በጣም ዝቅ ስላለ፤ ዜጎች የውጭ ምንዛሬ ሲፈልጉ የአገሪቱን ገንዘብ ወደ ባንክ የሚወስዱት በቅርጫት ነበር። ይህች አገር ብዙ ሙከራዎችን ካደረገች በኋላ ቢጨንቃት የአሜሪካን ዶላር መጠቀም ጀመረች። ዛሬ አንድ የአሜሪካ ዶላር በዝምባብዌ ዶላር ሂሳብ $361 ይታሰባል።

ቬኔዚዌላም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማት ይነገራል። ይህች አገር አንድ ሰስሞን በላቲን አሜሪካ ከበለጸጉ አገሮች መካከል አንዷ ነበረች። ይህ ሲሆን የአገር ኢኮኖሚ እርጋታ አይኖረውም። ሰው እምነት አይኖረውም። የውጭ ምንዝሬ እጥረት እያደገ ይሄዳል። መንግሥት ቁጥጥር ያከሂዳል።

ቁጥጥሩ ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም ተንኮለኞቹ ወይንም አትራፊዎቹ ከጥቁር ገበያው ትርፍ ስለሚያገኙበት ነው። ለምሳሌ፤ እኔ ለዘመዶቸ አንድ ዶላር ወደ አገር ቤት ለመላክ ብፈልግ፤ አንዱ ዶላር መንግሥት በተመነው መጠን ሕጉ በፈቀደው መንገድ ብልከው 37.6052 ብር ይሆናል ልበል። አንድ መካሪ አንተ ሞኝ አትሁን፤ እኔ አንዱን ዶላር በአርባ ብር እቀይርልሃለሁ ቢለኝ ምን ይሆናል? ይህን ሕገወጥ አማራጭ ካስተናገድኩ ትርፍ አገኘሁ ማለት ነው። አስቡት፤ በመቶ ዶላር የሚገኘው ትርፍ ምን ይሆናል? ከፍ ይላል ማለት ነው።

ላሳስብ የምፍልገው ቁም ነገር፤ ትርፍ ለማግኘት ዶላር ሆነ ሌላ የውጭ ገንዘብ ወደ ብር ከሕግ ውጭ ስንመነዝር የሚጎዳው ማነው ብለን የመጠየቅ ግዴታ አለብን የሚለውን ነው። እኔ አገር ወዳድ ነኝ ካልኩ፤ የአገሬን ኢኮኖሚ ለትርፍ ስል አልጎዳውም የማለት ግዴታ አለብኝ።

በቅርቡ አንድ ሃኪም “ገንዘብ ልልክ ነበር” አለኝ። “አይ ግሩም ነው፤ ላክ” አልኩት። “አየ ከፍ ያለ ምንዛሬ ለማግኘት ነበር” ሲለኝ፤ “አየ ጉድ፤ አንተማ እንዲህ ካደረግህ እንዴት ወያኔን እቃወማለሁ ትላለህ” አልኩት። አስቡት፤ ወያኔዎች በያሉበት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያዳክሙበት አንዱ ዘዴ የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ መቀየር ነው። እኛ የዚህ ተባባሪ ከሆንን፤ ተራውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጎዳነው ማለት ነው። መንግሥትን ብቻ አይደለም። ባንኮችን ብቻ አይደለም። የዋጋ ግሽፈትንም እየጨመርን ነው። ሙስናን እያጠናከርነው ነው። ይህ ብቻ አይደለም።

የጥቁር ገበያው እየዳበረ ሲሄድ የሚጠቀሙት ኃይሎች መሳሪያም ይገዙበታል። መሳሪያው ከህግ ውጭ ሲገዛ ሰላም፤ እርጋታና የሕግ የማስከበር አቅምም ይዳከማል። የንግድ ሚዛኑ እየተዛባ የውጭ ምንዛሬ አቅምም ደካማ ይሆናል።

ምን እናደርግ?

እኛ ከህግ ውጭ የምንሸምተው የውጭ ምንዛሬ (Transactions of foreign exchange in the Black Market) ምን ያህል እንደሆነ አላውቅም። ትኩረት የምሰጠው ግን ጉዳቱን ነው። ነጋዴው፤ ቱሪስቱ፤ ልጁንና ቤተሰቡን ውጭ ልኮ ድጎማ የሚሰጠው፤ ወገኖቻችን የምንደጉመው፤ ቤትና ሌላ ንብረት የምንገዛው፤ እርዳታ የምንለግሰው ወዘተ ተደማምሮ ሲታይ ከፍተኛ ጉዳት አለው። የውጭ ምንዛሬው በስዊስ ፍራንክ፤ በዶቸ ማርክ፤ በአሜሪካ ዶላር፤ በፈረንሳይ ፍራንክ ወዘተ ሊሆን ይችላል። ልውውጡ በአማካይ 30፤ 40፤ 45 በመቶ ቢሆን ጉዳቱን አስቡት።

የሶቭየት ሕብረት አለቃዎች (ልሂቃን) በ 1967 አንድ ዶላር በኦፊሲል ከሚቀየረው ከ0.9 ሩብል በላቀ ደረጃ በጥቁር ገበያ በ4.6 ሩብል ይቀይሩ ነበር። ይህ ግፍ ተራውን ሕዝብ ጎድቶታል፤ የአገራቸውን የውጭ ምንዛሬ መጠን አዳክመውታል። የግል ጥቅምና ስግብግብነት ታላቋን ሶቭየትን ተጠቂ እንድትሆን ግብዓት ሆኗል።

በጥቁር ገበያ ተበክላ የነብረችው ታንዛኒያ የገንዘቧን ዋጋ (value) በ800 በመቶ እንደቀነሰች ይነገራል። አንድ ሰሞን ብቻ የጥቁር ገበያው ከፍተኛነትና የዋጋው ግሽፈት 4000 በመቶ ንሮ ነበር። ጋና ልዩ ዘዴ ተጠማ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገጠማት። የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና ኩባንያዎች በአይነት ልውውጥ አያደረጉ እንደ ባቂላ ያሉ ጥራ ጥሬዎች ይሸምቱ ነበር። እትዮጵያ ወደዚህ ደረጃ አልደረሰችም። ሆኖም፤ የጥቁር ገበያው እንደጎዳት አምናለሁ።

የህወሓት የጥቁር ገበያ ሌብነትና ከሃገር ያሸሸው የውጭ ምንዛሬ መጠን ምን ያህል ይሆን?

ልዩ ልዩ ጥናቶችና ምርምሮች የሚያሳዩት መረጃ መልሱን ይሰጣል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም፤ ዓለም ባንክ፤ በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት እምቤኪ የተካሄዱ ሰፊ ጥናቶች ያሳዩት የማያሻማ መረጃ ኢትዮጵያ በሙስናና ከአገር ከሕግ ውጭ በተዘዋወረ ግዙፍ የሕዝብ ገንዘብና ኃብት ተጠቂ ከሆኑት አገሮች መካከል ከመጀመሪያዎቹ ጋር የምትታወቅ አገር መሆኗን ያሳያሉ። በተጨማሪ፤ ዴቪድ ስታየንማን የተባለው የፎርብስ ጋዜጠኛ “Money, Blood and Conscience” የሚል ትንተና ያቀረበው “Ethiopia’s Cruel Game,” የመጀመሪያው ሰነድ ስለ ንጹሃን እልቂት፤ በተለይ ዐማራውን በሚመለከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ስለ ዘረፋው መረጃ ይሰጣል። ሁለቱን ወንጀሎች የፈጸመው ህወሓት ነው።

ኢትዮጵያ ግዙፍ የውጭ እርዳታ ታገኛለች፤ ጠንካራና ታታሪ ሕዝብ አላት። ግን ለመልማት አልቻለችም “Why, despite ever-increasing amounts of foreign support, can’t this nation of 100 million clever, enterprising people feed itself? Other resource-poor countries facing difficult environmental challenges manage to do so.”

“ይህን ያህል እርዳታ እያገኘች ለምን ለመልማት አልቻለችም?” የሚለው ጥያቄ አግባብ አለው። መልሱ ቀላል ነው። አብዛኛው የእርዳታ ገንዘብ በህወሓትና በአጋሮቹ ተዘርፏል። ለምሳሌ፤ የአሜሪካ መንግሥት ብቻ ከ1991 በኋላ የለገሰው $30 billion (ቢሊየን) ሙሉ በሙሉ ተመዝብሯል። እስታየንማን እንዳስቀመጠው “The amount stolen by Ethiopia’s leaders since it took power is $30 billion.” This figure “is based on the UN’s own 2015 report on Illicit Financial Outflows by a panel chaired by former South African President Thabo Mbeki and another from Global Financial Integrity, an American think tank.

በየዓመቱ ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ ተሰርቋል? ከ$2-3 billion—an amount roughly equaling Ethiopia’s annual foreign aid and investment—being drained from the country every year, mostly through over- and under-invoicing of imports and exports.” ዋጋን በማጭበርበር (ማሳነስና መቀነስ)፤ የውጭ ምንዛሬን በውጭ አገር በማስቀረት ወዘተ የሚደረግ የኢኮኖሚና የፋይንናስ ወንጀል ነው። በየዓመቱ በዝቅተኛ ሁለት ቢሊየን ዶላር ከሸሸ ህወሓት ኢትዮጵያን በበላይነት በገዛበት ዘመን ተሰርቆ ከሃገር የሸሸው የውጭ ምንዛሬ መጠን ከአምሳ ቢልየን ዶላር በላይ ይሆናል።

ለመሆኑ ሰፊው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ፤ በግምት ሁለት ሚሊየን ነው ተብሎ የሚገመተው በዐመት በሃዋላ (Remittances) ስንት ዶላር ይልካል? ዓለም ባንክ የሚሰጠውን ግምት በምንም አልቀበልም። የምቀበለው ዓለም አቀፍ የማይግራንት ድርጅት (International Office for Migration/IOM) በ2014/2015 ያከናወነውን ጥናት ውጤት ነው። በዚህ ድርጅት ጥናት መሰረት፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሬሚታንስ የምታገኘው ኦፊሴል መጠን $2.7 ቢልየን ዶላር ነው። ይህም ማለት ከጠቅላላ የአገር ገቢዋ 5 በመቶ መሆኑ ነው። የዓለም ባንክን ብቀበል ኖሮ፤ 0.60 ይሆናል። ተመልከቱ ያለውን ልዩነት።

ይህም ሆኖ የአይኦኤም ጥናት ያሳስበኛል። ለምን? ምክንያቱም፤ ወደ ሶስት ቢልየን ዶላር በዓመት የሚለው በኦፊሴል የሚገባው ብቻ መሆኑ ነው። ሰባ ስምንት (78 በመቶ) የሚሆነው ዲያስፖራው ወደ አገር የሚልከው የውጭ ምንዛሬ የሚላከው በጥቁር ገበያው ነው (Through the so called the informal sector):: ከላይ ሃኪሙ ከኦፊሴሉ ውጭ ዶላር የሚቀይር መሆኑ ነው። በዚህ ዘዴ ደግሞ የተካኑት ህወሓቶች ናቸው። መቶ በመቶም ባይሆን ቢያንስ ከሰማንያ በመቶ (80 %) ለመሸጋገር ብንጥር እኮ ከፍተኛ በረከት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አበረከትን ማለት ነው። እስኪ፤ ባራክ ኦባማ እንዳሉት “እኛም እንችላለን” እንበል።

ዘራፊዎች በሃላፊነት ይጠየቁ።

ህወሓት በሕግ መጠየቅ ያለበት በክህደት፤ አገርን በማፈራረስና በሕዝብ እልቂት ብቻ አይደለም። በምዘበራም መከሰስና የተዘረፈው የኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ኃብት እንዲመለለስ መደረግ አለበት። ሃላፊነት ማለት ይኼም ጭምር ነው።

ዘራፊዎቹ እነማን ናቸውና የዘረፉት ግዙፍ ኃብት የት ተደበቀ? የሚሉት ጥያቄዎች ለትንትናየ ፋይዳ የላቸውም። ከዚህ በፊት ጠቁሜ ስለነበር አልደግማቸውም።

ለማጠቃለል፤ እባካችሁ፤ እኛ አገር ወዳድ ነን የምንል ግለሰቦች የህወሓትን የሰለባ ባህል አንከተል። ማንኛውንም ወደ አገር ቤት የምንልከውን የውጭ ምንዛሬ ሕጋዊ በሆኑ መንገዶች ብቻ አናሰተላልፍ። ቁርጠኛነት ማለት መሳሪያ ይዞ መዋጋት ብቻ አይደለም።

ከዛሬ ጀምሮ አደራ የምላችሁ፤ ከራስችን ቤተሰብ፤ ዘመድ አዝማድ ጀምረን፤ ወዳጆቻችንን ሁሉ በያሉበት እየመከርን የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ አትቀይሩ ነው። ሕግ ይከበር እያልን ሕግን የማስከበር ግዴታችንን እንወጣ። የኢትዮጵያን ጀግናና ታታሪ ሕዝብ እንታደግ። ኢትዮጵያ መመካት ያለባት በልመና ሊሆን አይችልም።

ኢትዮጵያ ራሷን የመቻል እምቅ አቅም አላት። ዲያስፖራው የዚህ ታሪካዊ ተልእኮ አካል እንዲሆን አደራ አላችኋለሁ።


ኢትዮጵያንና መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አምላካችን ይባርክ!!

12;/4/2020

Featured Posts
Recent Posts
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Classic
  • Twitter Classic
  • Google Classic
bottom of page