ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ
- Abebe Gelagay
- Jul 31
- 2 min read

ከጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ 7/27/2025
ታሪክ እንደሚመሰክረው በየጊዜው የሚፈራረቀው የሱዳን መንግሥት ኢትዮጵያ የውስጥ ችግር አለ ፤ ትኩረቷ ወደ ውስጥ ነው ብሎ ባሰበ ጊዜ ዳር ደንበራችንን እየተሻገር በርካታ ወረራዎችን ፈጽሟል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር 2020 ወያኔ ከአማራ ጋር ሒሳብ አወራርዳለሁ ፤ ኢትዮጵያን አፈርሳልሁ ብሎ ጦርነት ሲጀመር የሱዳን መንግሥት እንደለመደውና ድሮም እንደሚያደርገው በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በምድረ ገነት በኩል (እነሱ አልፋሽጋ) ብለው በሚጠሩት ደንበር ጥሶ በመግባት የኢትዮጵያን ገበሬዎች ገድሎ ፤ ሀብት ንብረታቸውን ቀምቶ የቀረውንም አቃጥሎ ከእርሻቸውና ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ካደረገ በኋላ መሬቱን የራሱ ገበሬ እንዲጠቀምበት አድርጎታል፡፡
ይህን አስመልክቶ ጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት በወቅቱ የጉዳዪን አሳሳቢነት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መሬታችን ለማስመለስና ደንበራችንን ለማስከበር ምንም አይነት እርምጃ ሲወስድ ባለመታየቱ ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን ተስፋ እንዲያጣ አድርጎታል። የሀገር ሉዓላዊነት አምስት ዓመት ሙሉ በባዕድ ሀገር እና መንግስት ሲደፈር መንግሥት ዝምታን መምረጡ ለህዝቡ ግልጽ አይደለም፡፡ ስለሆነም፤
መንግስት የሀገር ሉዓላዊነት የማስከበር ግዴታውን በአስቸኳይ እንዲወጣ ፤ በንቀትና በድፍረት ሀገራችን ውስጥ ገብቶ የሰፈረውን የሱዳንን ጦር በአስቸኳይ እንዲያባርር።
አምስት ዓመት ሙሉ እየተንገላታ ያለስራ የተቀመጠውን ገበሬ ወደ ቦታው ተመልሶ እንዲሰፍር እና ሀገራዊ ልማቱን እንዲያፋጥን።
ከስራውና ከልማቱ ተናጥቦ የቆየውን ገበሬ መንግስት ማካካሻ፣መደጎሚያ እና ማበረታቻ እንዲሰጠው።
በተጨማሪም ፤ ኢትዮጵያ የተወረረባትን መሬት አስመልሳለች የሚል ዜና በተለያዩ የዜና ውርታሮች ሰምተን ተስፋችን እየለመለመ ባለበት ሰዓት በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምንም አዲስ ነገር የለም የሚል ማብራሪያ መስጠቱ አሳስቦነል። ሱዳን ትሪቡን ደግሞ የኢትዮጵያ ሚሊሻ በአልፋሺጋ በኩል ትንኮሳ አድርጓል የሚል ዜና ከትቧል ታዲያ በኢትዮጵያ በኩል ምንም አዲስ ነገር የለም መባሉ ለምን ይሆን?
የሆነ ሆኖ ጎንደር ህብረት ፤ መንግስት መቸ ነው ደንበራችንን የሚያስከብረው የሚል ጥያቄ ለማንሳት ተገዷል። እንዲሁም ድርጅታችን የሀገር ሉዓላዊነትን ፣ የህዝብ ደህንነትን ማስከበር እና ማክበር የመንግሰት ተቀዳሚ ተግባርና ግዴታ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለው።
ስለዚህ ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ እና ሳይውል ሳያድር በድርድርም ሆነ እነሱ በመጡበት መንገድ መሬታችን እንዲመለስና ደንበራችን እንዲከበር አጥብቀን እንጠይቃልን፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻችን በደም እና ባአጥንታቸው አስከብረውት ያቆዮትን ሀገር ፣ ያስከበሩትን ደንበርና ወሰን ለተተኪው ትውልድ የማስረከብ አድራ፤ መንግስት ሐላፊነቱን እንዲዎጣ እናሳስባለን። አባቶቻችን ያስቀመጡልንን ወሰን እንጠብቃለን። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።


















Comments