top of page

እባብን በእንጭጩ

www.gonderhibret.org

4126 Deerwood Trail, Eagan MN 55122 Tel 651 808 3300

ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ. ም.(06/17/2021)

እባብን በእንጭጩ

በቅርቡ በጎንደርና በማዕከላዊ የጎንደር ዞኖች የደረሰው፣ ጎንደርን የጦርነት ቀጠና ያስመሰለው ሁኔታ በጣም የሚያሳዝንም የሚያስቆጣም ነው። የብዙ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል። ንብረት አውድሟል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ተፈናቅለው ተበትነዋል። የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ ሲቻል ችግሮች በራሳቸው ብን ብለው ይጠፉ ይመስል መንግሥት በቸልተኝነት ስለተመለከታቸው ነው። ባለፉት ወራት እራሱን የቅማንት ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው የህወሓት/ትህነግ ተላላኪ ኮሚቴ በጭልጋ በኋላም በጎንደር ዙርያ ያደረሰው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የገቢያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ ይህን ተከትሎ ተራ ወንበዴዎች የፀጥታውን መደፍረስ ተጠቅመው ልዩ ልዩ ወንጀለሎችን ፈጽመዋል። ንፁህ ዜጋን አግቶ ገንዘብ ማስከፈል በየእለቱ የሚፈፀም ወንጀል ሆኗል። ይህ የሕዝብ ውክልና የሌለው እራሱን የቅማንት ኮሚቴ እያለ የሚጠራው ተላላኪ ቡድን አሁንም በአማራውና በቅማንቱ ማህበረሰቦች መካከል ግጭት ለማስነሳትና በተለይ ጎንደርን በማያቋርጥ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ አስገብቶ በድህነት ለማቆየት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያ-ጠል ድርጅቶች ትልቅ መሳሪያ ሆኖላችዋል። ተጋብተው-ተዋልደው፣ ተጎራብተው፣ በዘር፣ በባህል፣ በቋንቋና በሃይማኖት ተጋምደው፣ በታሪካቸው ከማንም የበለጠ በሰላም አብረው የኖሩትን የቅማንትንና የአማራን ማህበረሰቦች በማጋጨት ለማትረፍ የተሸረበው ሴራ አሁንም ለትህነግ/ህወሓት እና አጃቢ ድርጅቶች ትርፍ እያስገኘላቸው ነው። ጎንደርን ከልማት ተርታ አውጥቶ የቆየው ሁኔታ እንዲቀጥልም እያደረገ ነው።


በቅርቡ በጭልጋ አይከል የዜጎቻችን መሞት፣ መፈናቀልና፣ የንብረት መውደም መድረሱ በጣም አሳዝኖናል። ይባስ ብሎ የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግሥታት ስለሁኔታው ለሕዝብ ባለመግለፃቸውየተጎዳው ሕዝብ እርዳታ እንዳይደርስለት ሆኗል። ከሁሉም በላይ እነዚህ አሸባሪ ሃይሎች ጭልጋ እንደገቡ የመንግሥት አካሎች ምንም እርምጃ ባለመውሰዳቸው ይህ ሁሉ ጉዳት መድረሱ የመንግሥት አካሎች ሚና ግራ የሚያጋባ ሆኗል። ከልዩ ኃይሉ ሌላ የመከላከያ ሠራዊታችን ካምፕ ከተማው አጠገብ እያለ እንዴት ቢደፍር ነው ይህ ቡድን ከተማውን እንዲያ ማተራመስ የቻለው? በዚህ ጥያቄ ላይ የመንግሥት ፖሊሲ ምንድን ነው? አንድ ቀን ብን ብለው በራሳችቸው ይጠፋሉና ዝም ብለን እንያቸው ነው?


ጭልጋ በደረሰው ሁኔታ የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ትምህርት ሆኖት የአካባቢው ፀጥታና ሰላም ይጠበቃል ብለን ተስፋ ስናደርግ ይባስ ብሎ በጎንደር ከተማ አካባቢ የደረሰው ተመሳሳይ ጉዳት አስገርሞናል፡ እነዚህ ተራ ወንጀለኞች ይህን ያህል ጉዳት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ አደጋ ለማድረስ መቻላቸው፣ መንግሥት የለም የሚያሰኝ ነው። በጎንደር ዙርያ ከፍንጭ በላይ የሆኑ መረጃዎች እየታዩ እንዴት እርምጃ አልተወሰደም?

ይህ ጎንደርን በየጊዜው እየተመላለሰ የዜጎቻችንን ህይወት የሚቀጥፍ፤ ንብረት የሚያወድምና ሰላም የሚነሳ ሁኔታ ጎንደርን የድህነት እስረኛ የስጋት አረንቋ እያደረጋት ነው። እንዴት ያለ ባለሃብት ነው ጎንደር ውስጥ ገብቶ ኢንቬስት የሚያደርግ፧ እንዴት ብሎ ነው ለወጣቱ የሥራ መስክ የሚከፈተው? ይህ ሰቆቃ መቆም አለበት። ስለሆነም የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የሚከተሉት እርምጃ በክልሉና በፌደራል መንግሥታቱ እንዲወስዱ አጥብቆ ይጠይቃል።


1/ ከመተማ እስከ ጎንደር ያለውን ቀጠና በተደጋጋሚ ሰላም የነሳውን የቅማንት ኮሚቴ በመባል የሚታወቀውን ኮሚቴና ደጋፊዎች ከዚህ በፊት በእርቅና በምህረት የገቡትንና ቃላቸውን የጠበቁትን ክልሉ አክብሮ፣ ቃላቸውን ያልጠበቁ በተደጋጋሚ በደረሱት ማጥቃቶች ላይ የተሳተፉን በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ።በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ሰፊ የማያዳግም የማፅዳት እርምጃ እንዲወሰድ፤

2/ በክልሉ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ስለ ወንጀለኞች እንቅስቃሴ መረጃ ደርሷቸው እርምጃ ያልወሰዱና የክልላቸውን ፀጥታ ለመጠበቅ ያልቻሉ ሹማምንት፣ ለምን ሃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ በሕጋዊ መንገድ ተጣርቶ እርምጃ እንዲወሰድ፤

3/ የክልሉ መንግሥት የደህንነት መዋቅሩን በእነዚህ አካባቢዎች እንዲያጠናክር፣ በሌለበት እንዲዘረጋ፤

4/ የፀጥታ ማስከበር እርምጃዎች ሲወሰዱ መንግሥት ሃላፊነቱን ወስዶ በፀጥታ ማስከበር ላይ የሚሰማሩ ላይ ቁጥጥር እንዲኖረው ማለትም አላስፈላጊ የሆኑ ሃይሎች እንዳይሳተፉ፣ ተሳታፊዎች ሁሉ ደግሞ በማዕከላዊ እዝ ሰንሰለት መዋቅር ውስጥ የገቡ ብቻ እንዲሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ቁጥጥር እንዲያደርግ፤

5/ የውጭና የአገር ውስጥ ድርጅቶችና ሕዝቦች ለተጎዳው ወገናችን ሊደርሱ የሚችሉት ስለደረሰው ጉዳት ሲያውቁ ስለሆነ በጭልጋና በጎንደር ዙርያ የደረሰው ጉዳት ለህዝብ ይፋ እንዲሆን፤

6/ ለተጎዳው ሕዝብ የፌደራሉና የክልሉ መንግሥታት ባስቸኳይ የመጠለያና የምግብ እርዳታዎችን እንዲያደርጉ፤

ችግሩ እራሱን በራሱ ይፈታል ብሎ መጠበቅ ወይንም ለነገ መቅጠር ለትውልድ የሚሻገር ቀውስ ማውረስ ይሆናልና ሳይውል ሳያድር የፌደራሉና የክልሉ መንግሥታት ከሕዝብ ጋር በተለይም ከቅማንቱና ከአማራው ማህበረሰብ ሽማግሌዎች ጋር ተባብረው ለጥያቄው የማያዳግም መፍትሄ እንዲሰጡ አጥብቀን እናሳስባለን።


ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!


የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት

Featured Posts
Recent Posts
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Classic
  • Twitter Classic
  • Google Classic
bottom of page