ዜና እረፍት

ጥር 10 1949፟ - ነሓሴ 9, 2013
አቶ ዳዊት (አዳነ) ሙጨ ከአባታቸው ከአቶ ሙጨ ተገኘና ከእናታቸው ከወ/ሮ የሮምነሽ መኮነን እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 10 1949 ዓ ም በጎንደር ከተማ፣ በገብርኤል ቀበሌ ተወለዱ። አቶ ዳዊት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በልዕልት ተናኘ ወርቅ ያጠናቀቁ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአፄ ፋሲል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተከታተሉ ነበር። በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃትና በትጋት ተካፋይ በመሆናቸው ኢ ሕ አ ፓን በአባልነት ተቀላቅለው ትግሉን ቀጠሉ። መንግሥት የደረሰበትን የፖለቲካ ተቃውሞ በኃይል ለመደምሰስ በወሰደው እርምጃ ብዙ የጎንደር ወጣቶች ሲረግፉና ሲሳደዱ አቶ ዳዊትና ታላቅ ወንድማቸው አቶ ሲሳይ ሙጨ ከዚህ አላመለጡም። መንግሥት ከበባ አድርጎ ታላቅ ወንድማቸው አቶ ሲሳይ ሙጨ ሲሰዉ፣ አቶ ዳዊት ለማምለጥ ችለዋል። አቶ ዳዊት ከዚህ የከተማ ግዲያ እንዳመለጡ ወዲያውኑ ወደ ገጠር በመውጣት የኢ ሕ አ ፓን ሠራዊት ኢ ሕ አ ሠን በመቀላቀል ትግሉን ቀጠሉ።
በሠራዊቱ ውስጥም በተለያየ ደረጃ የሰሩ ሲሆን በመጨረሻ የኃይል ኮሚሳር በመሆን አገልግለዋል። በእንዲህ እያሉ የኢሕአሠ ሠራዊት ከአርማጭሆ ወደ ሽንፋ ወንዝ ለመዉረድ በወሰነበት የመጨረሻዎቹ ወራት፣ አቶ ዳዊት ሙጨ በወፍ በሽታ በመታመማቸው የነበሩበትን ኃይል እንቅስቃሴ በፖለቲካ ኮሚሳርነት በመምራት ሊቀጥሉ አልቻሉም። ስለዚህም የሠራዊቱ ጊዜያዊ አመራር ኮሚቴ አቶ ዳዊት የተሻለ ህክምና ወደ ሚያገኝበት ወደ ሱዳን ከሌሎች በሽተኛ ጓዶች ጋር እንዲወጡ አድርጓል። በሰራዊቱ ውስጥ በነበሩበት ጊዜያት አቶ ዳዊት በፖለቲካ ንቃታቸውና ሁኔታዎችን በማስረዳት ረገድ በሁሉም ጓዶቹ የተመሰገኑና የተከበሩ ነበሩ።
እንደ ብዙ ጓዶቹ ሱዳን ውስጥ ለጥቂት ጊዜያት ከቆዩ በኋላ በአሜሪካ የማስፈር ፕሮግራም ተሳታፊ በመሆን ወደ አሜሪካ ተጓዙ። አሜሪካ በቆዩባቸው አመታት ውስጥ በኢሊኖይ ኢንስቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (ITT) በኤሌክትሪካል መሃንዲስነት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ አቶ ዳዊት በአገር ጉዳዮችና በኢትዮጵያውያን የማሕበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ በመሳተፍ ሁልጊዜም ለአገር ያላቸውን ተቆርቋሪነት ለኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ያሳዩ፣ ለጋስ፣ ለሰው አዛኝ፣ ለአገር ተቆርቋሪ ለጥቅማ ጥቅም የማይታለሉ ኩሩ ወንድም ነበሩ።
አቶ ዳዊት በአገራችን ሁኔታ ባለፉት አምስት አመታት አስተዋጽዎ ካደረጉባቸው ድርጅቶች ውስጥ አጉልተን የማናስቀምጠው በጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ የተጫወቱትን ሚና ነው። አቶ ዳዊት የድርጅት ጉዳይ ኮሚቴውን በመምራት ወጣቶችን ወደ ድርጅቱ ለመሳብና ለማደራጀት ትልቅ ጥረት አድርገዋል። እንዲሁም የእትመትና የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል። የጎሕ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል በመሆን ሰርተዋል።
በሁለተኛው ጉባኤ የጎንደር ሕብረት የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ሆነው ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ ታመው እስከተኙበት ቀን ድረስ በትጋትና በብቃት ሰርተዋል። በስራ አስኪያጅ ስብሳባዎች ሁሉ በሚያቀርቧቸው ሃሳቦችና ስለ አገራችን ሁኔታ በሚሰጧቸው ትንተናዎች ተደማጭነት ነበራቸው። ወቅታዊ ጉዳዮችንና መረጃዎችን በመተንተን ያልደፈርሰና ሚዛናዊ የሆነ ትንተና ያቀርቡ ነበር። ማብራሪያ በማቅረብና ለጥያቄዎች መልስ በመስጠት በጥሩ አንደበት ሃሳባቸውን በመግለጽ አሳማኝና ተሰሚነት ነበራቸው።
አቶ ዳዊት ህገር ወዳድ የማያውላውል ቁርጠኛና ወደኋላ ሳይሉ ለሕዝብ መብት፣ ለሃገር ልዕልናና ለህገር ብልጽግና ህይወታቸውን በሙሉ መስዋእት ያደረጉ ጥሩ ዜጋ ሲሆኑ ክሰው ጋርም ተግባቢ፣ ቅን፤ ለጋስ፣ ታማኝና አስተዋይ ነበሩ።
አቶ ዳዊት ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሚኖሩበት ቺካጎ ከተማ ሲታከሙ ከቆዩ በኋላ ወደ አገራቸው እንዲወሰዱ በጠየቁት መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው በአዲስ አበባ ህክምና ላይ እንዳሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል። አቶ ዳዊት በሕይወት ጊዜያቸው ያበረከቱትን አስተዋጽዎ እየዘከርን የዘለዓለም ሕይወት ያውርስልን እያልን እንሰናበታቸዋለን።
ለቤተሰባቸውና ለወዳጆቻቸውም እግዚአብሔር መጽናናቱን ይስጥልን።