top of page

የማይታለፍ እድልና ድል

የማይታለፍ እድል እና ድል

ለጎንደር ኅብረት እና ለጎንደሬዎች ከተስፋሁን /አትላንታ

ውድ ወገኖቼ በዝች አጭር ጽሁፍ ብዙ አዲስ ነገሮችን አቀርባለሁ አልልም ግን በየቤታችን የምናነሳቸውን ነጥቦች ጠቅለል አድርጌ በማስቀመጥ ትኩረት እንድንሰጥባቸውና በፍጥነትም እንድንቀሳቀስ ግፊት ለማድረግ የበኩሌን እና የሚሰማኝን ለመግለጽ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ የጎንደር ህዝብ ከ1972 ዓ/ም ጀምሮ ያሳለፈው ችግር በታሪኩ በልዩ መዝገብ የሚቀመጡ የመከራ ዘመን ነው። የሰሜን ጎንደር አራት ወረዳዎች ከወገራ ሶስቱ ወልቃይት ጠገዴ እና ሰቲት ሁመራ ከሰሜን ፀለምት የተወለዱት ወገኖቻችን ከ40 ዓመት በላይ በትውልድ ቀያቸው የመኖር መብት አጥተው ከሃገር አልፎ በዓለም እንዲበተኑ ተገደዋል። ይህ በወያኔ(ትህነግ) የተፈጸመ ግፍ የተደረገ ዘረፋ ፍጹም-ፍጹም የሚረሳ እና ይቅር የሚባል አይደለም። ወያኔ እነዚህን ቦታዎች ለመያዝ የተጠቀመችበት ስበብ ትግረኛን በተደራቢነት ይናገራሉ፤ ስለዚህ ትግሬዎች ናቸው የሚል ማስመሰያ ተረት ተረት ይሁን እንጅ በዋነኛነት ምክንያቱ የመሬቱ ለምነት እና ከሱዳን ጋር ያለው ኩታገጠም መዋሰን ያለውን ጥቅም በማሰብ እንደሆነ በሰፊው ሲነገር ቆይቷል። አዎ ይህ ትክክል አባባል ነው ሆኖም ይህን ድፍረት እንዲያስቡ ያደረጋቸውን ዋና ጉዳይ በደንብ ስንነጋገርበት አይሰማም። “የብሄር” ክልሉ ትግረኛ በመናገር ላይ የተቃኘ ነው የሚሉማ ቢሆን ኖሮ ወያኔ ስትመሰረት ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች ኤርትራ ውስጥ ደግሞ ትግረኛ መናገር ብቻ ሳይሆን በዘር ግንዳቸው ከትግራይ የሚወለዱ በርካታ ወገኖች በሰፊው በኤርትራ ውስጥ ሰፍረዋል። ታዲያ ወያኔ እነዚህን ወገኖች የብሄሬ አባላት ናቸው በትግራይ መካለል አለባቸው አላለም፤ መረብን ተሻግሮም ያቀረበው የክልል ጥያቄ አልነበረም ያውም የአያቶቹን ግዛት፤ ግን ለምን ጎንደርን እንደዚህ ተዳፈረ? ለምን ኤርትራንስ አልሞከራትም?

በኔ እምነት የዚህ ጥያቄ መልስ ነው ይህን ያህል ዘመን ጎንደሬዎችን እንድንሰቃይ ያደረገን፤ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንም እንድናጣ ያደረገን፤ መረብን ተሻግረው ያባቶቻቸውን ግዛት ለማስመለስ ያልሞከሩት ወያኔዎች ተከዜን ተሻግረው ይህን ሁሉ ግፍ ሲፈጽሙ ይህን ሁሉ ዘረፋ ሲያካሂዱ አዲስ ካርታ ሲቀርጹ ዋናው ምክንያት በኤርትራ ውስጥ በመሳርያ ትጥቃቸው የሚገዳደሩ የታጠቁ እና የተደራጁ ኤርትራዊ ድርጅቶች ስለነበሩ ነው። በጎንደር ግን የነበሩት ህብረ ብሄር ድርጅቶች ከደርግ እና ከወያኔ ይደረግባቸው ከነበረው ተከታታይ የተቀናበረ ጥቃት ጋር የውስጥ ችግራቸው ተጨምሮ አቅማቸው ተዳክሞ ከአካባቢው በመራቃቸው ወያኔ(ትህነግ) ከፍተኛ እድል አገኘ። ይህንም ስል የአካባቢው ተወላጅ በመሆኔ በአካባቢውም ስለነበርኩ ብዙ መመስከር እችላለሁ። ህዝባችን ወያኔን ቀጤማ ጎዝጉዞ አልተቀበለውም በጀግንነት ብዙ መስዋእትነት በመክፈል ታግሏቸዋል። በጊዜው የነበረው የደርግ መንግስት ምንም እርዳታ ሳይሰጠው በራሱ ትጥቅ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ወያኔን ከቀየው ላለማስገባት ብዙ ተዋግቷል ብዙ ጀግኖች ተሰውተዋል።

“ማረሻው ምንሽር መጎልጎያው ጉዋንዴ

ያባደፋር አገር ወልቃይት ጠገዴ “

እያለ ብዙ መስዋእትነት ከፍሏል፤ ሆኖም ይህ ሁሉ ህዝብዊ ትግል በተደራጀ መልክ አለመሆኑን የተረዳው ወያኔ የትግሉን አንቀሳቃሾች እና ተሰሚነት ያላቸውን ባላባቶች(ያካባቢው ተወላጆች) እያፈነ በመውሰድ መግደል እና ማጥፋት በመቀጸሉ ለመቋቋም ከባድ ነበር፤ ቦኋላ ግን ትግሉን በተሻለ መልክ ለማካሄድ እንደነ ከፍኝ እና የአርበኞች ግንባር አይነት ድርጅቶችን መስርቶ የታገለውም የዚህ አካባቢ ህዝባችን ነው።

ደርግ ወድቆ ወያኔ(ትህነግ) መንበረ-ስልጣኑን ከያዘ ቦኋላ ወልቃይትን እና ሰቲት ሁመራን ሙሉ በሙሉ ጠገዴን እና ጠለምትን በከፊል በማናለብኝነት ከትግራይ ጋር ማካለል ብቻ ሳይሆን በማስገደድ “ትግሬ” ናችሁ በማለት የህዝቡን ባህል እና ቋንቋ ለማጥፋት ከመሞከሩም በላይ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን አምጥቶ በማስፈር የአካባቢውን ተወላጆች ከትውልድ ቀያቸው በማፈናቀል ለስደት ዳረጋቸው። ዛሬ ኦሃዮ መሄድ ማለት አውስትራሊያ መሄድ ማለት ሱዳን መሄድ ማለት ወልቃይት መሄድ እስኪመስለን ድረስ ህዝባችን የማያውቀውን ስደት ህይወት አድርጎ እንዲኖር ተገዶ ቆይቷል። እስኪ አስቡት የኛ ህዝብ ድሮ እንኳንስ ይህን ያህል እርቆ ለመሰደድ ይቅርና ከጠገዴ ወደ ሁመራ ሄዶ ለማረስ እንኳን ፈቃደኛ አልነበረም ከትውልድ ቦታው ጋር የነበረው ቁርኝት በምንም ጥቅም የሚለወጥ አልነበረም፤ የወያኔ ግፍ እና መከራ ግን አትላንቲክን አቋርጦ ሕንድ ውቂያኖስን ተሻግሮ እንዲሰደድ አደረገው፤ ሰባት ቤት ቆጥሮ ወገኔ ጋር አንለያይም ማለት ቀርቶ አባት እና ልጅ እህትና ወንድም ለረዥም ጊዜ ተለያዩ ፤ ከወያኔ ግፍ ህይወትን ለማዳን ያችን የሚወዱዋትን አገር ለቆ እድሜን ሙሉ በሰው ሃገር መንከራተት ያለፈው 40 ዓመት ታሪካችን ሆነ። መቼም ይህ የመከራ ዘመናችን እንዲያልፍ ከፍተኛውን መስዋእትነት የከፈሉትን ወገኖቻችን ማንሳት ደስ የሚል ቢሆንም ይህን ለሌላ ጊዜ በማስቀመጥ ወደ ተነሳሁበት ሃሳቤ ተመልሼ ሃሳቤን ጠቅለል አድርጌ ላስቀምጥ።

አሁን ሃገራችን ያለችበትን ሁኔታ መዘርዘር ብዙ የሚጠብቅብኝ አይመስለኝም፤ ወያኔ ባለፉት አርባ አመታት የሰራው ግፍ ከተፈጥሯዊ ባህሪው የመነጨ መሆኑ ተጋልጦ እርቃኑን መቅረቱን ጎንደሬዎች እና ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ዛሬ ዓለም የሚናገርበት ወቅት ሆኗል። ከብዙ መስዋእትነት ቦኋላ ወያኔ ከአካባቢያችን ተፈንቅሎ ሲባረር የፈፀመው ዘር የማጥፋት ወንጀል በታሪካችን ጎልቶ የሚታይ ጥቁር ነጥብ ነው። አሁን አካባቢው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ሁላችንም እናውቃለን፤ ታዲያ ምን ማድረግ ብንችል ነው በአስተማማኝ ያገኘነውን እድል እና ድል ዘላቂ ማድረግ የምንችለው በሚለው ሃሳብ ላይ መነጋገር እና መስማማት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ የሚከተሉትን እላለሁ።

1ኛ- የጎንደር ተወላጆች ከምንጊዜም በላይ በመቻቻል እና በመሰባሰብ ተጠናክረን መውጣት ግድ ይለናል፤ ለዚህም ብዙዎቻችን የተሳተፍንበት የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ለትግሉ አስተዋፀኦ ሲያደርግ የቆየውን የ ጎንደር ኅብረትን አጠናክረን ማውጣት ከምንጊዜም በላይ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው። አዎ የተለያዩ ቅሬታዎችን ወይም ድክመቶችን የሚያነሱ ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ ግን ምንም ይሁን ምን የጎንደር ኅብረት ለጎንደር ክብር እና ለጎንደሬዎች አንድነት የሰራውን ትልቅ ስራ ልንንቀው አይገባም፤ የተመረጡትም ወገኖቻችን የሚችሉትን ያህል አድርገዋል። በጊዜው በነበረው መንግስታዊ ቁጥጥር እና ተፅእኖ ከዚያ በላይ ለመሄድ የሚያስችል ሁኔታ ስላልነበረ የጠብቅነውን ያህል ስራ ባይሰራም ልንፈርድባቸው አንችልም። አሁን ግን ሰፊ በጣም ሰፊ እድል ተከፍቷል ይህን እድል ሳንጠቀምበት ብንቀር እጅግ እጅግ የሚያሳዝን ይሆናል፤ ስለዚህ ልባችን ከምንጊዜም በላይ አንቅተን ሆዳችን ከምንጊዜም በላይ አስፍተን በመቀራረብ እና በመወያየት ጎንደር ኅብረትን አጠናክረን ትልቅ ስራ መስራት ግድ ይለናል። የጎንደር ኅብረት መሪዎችም

1.1 በጎንደር ዙሪያ የተደራጁ ሃይሎችን ሁሉ በማነጋገር በጋራ ለመስራት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባችኋል።

1.2 በያካባቢው የነበሩትን እና ያሉትን ቻፕተሮች በፍጥነት በማነጋገር ለጥያቄዎቻቸው መልስ በመስጠት ክፍተቶቹን በመሙላት ድርጅቱን አጠናክራችሁ ለማውጣት መንቀሳቀስ ይገባችኋል።

1.3 ይህ ወቅት ከምንጊዜም በላይ ለጎንደር እና ለረዥም ጊዜ ለተሰቃየው ጎንደሬ ጠቃሚ ስራ የሚሰራበት ወቅት ከመሆኑም በላይ ጎንደርን ወደነበረችበት ደረጃ ለመመለስ ጠቃሚ ስራ የሚሰራበት ምቹ ጊዜ በመሆኑ አስቸኳይ ኮንፈረንስ (ቢያንስ ለሁለት ቀን} በማዘጋጀት ጠቃሚ ሃሳብ የሚያቀርቡ ተወላጆችን በመጋበዝ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ አገር ቤት የሚካሄደው ትግል የአይነት ለውጥ እንዲኖረው የምናደርግበትን ስራ መስራት ግድ ይላችኋል (አደራ ኮቢድ 19 እንዳታመካኙ ይህን ትልቅ እድል አለመጠቀም ዋጋ ያስከፍላል)።

1.4 በአካባቢያችን በአማራነታቸውም ሆነ በሌላ መልክ ወይም በኢትዮጵያዊነት ከተደራጁት ወገኖቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር የተቀናጀ ስራ ለመስራት እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባችኋል።

1.5 የተገኘው እድል እና ድል ትርጉም ያልው ለውጥ እንዲያስገኝ በህዝባችንም ህይወት ላይ እንዲንፀባረቅ በኅብረተሰባችን ውስጥ አንድ አይነት አመለካከት እንዲኖር ያስፈልጋል። ለዚህም ጎንደር ኅብረት ህብረተሰቡን በልዩ ልዩ መልክ አደራጅቶ ዘርፈ ብዙ ስራ ለመስራት እራሱን ማዘጋጀት አለበት። ለዚህም እውቀት ፤ ብቃት እና ህልም ያላቸውን የጎንደር ልጆች በማሰባሰብ ተሸጋጋሪ ስራ ለመስራት በድፍረት መንቀሳቀስ ይኖርበርታል።

2ኛ- እኛ እኛ በጎንደሬንታችን እንኮራለን የምንል እድሜያችን በሙሉ በወያኔ ጭካኔና ተንኮል ስንሰቃይ የኖርን ዛሬ ያገኘነውን እድል ልንጠቀምበት ይገባል። የወልቃይት ጠገዴ የጠለምት እና የሰቲት ሁመራ ባጠቃላይ የጎንደር ህዝብ መከራ እና በደል ሲቆጨን እና ሲያንገበግበን የቆየን ወገኖች ሁሉ አለመደራጀታችን ከአርባ አመታት በላይ ዋጋ አስከፍሎናል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን አሳጥቶናል፤ ለብዙ አመታት በስደት እድሜያችን አስጨርሶናል። በህይወት ለቆየነው ሰዎች አሁን የተገኘው እድል ትልቅ ስጦታ ነው። ይህን እድል ለመጠቀም ደግሞ ትልቅ መሳሪያ ድርጅት ነው። ድሮ ያልነበረን አሁን ግን በእጃችን ያለውን ወርቅ እንደ መዳብ አንቁጠረው ጎንደር ኅብረትን። ይህን ድርጅት ድርጅታችን አድርገን እንጠቀምበት ከተከዜ እስከ አባይ ያለውን ህዝብ ሊወክል የሚችል። ለዚህም ህዝብ ያቅሙን ሲወጣና ሲወርድ የቆየ ድርጅት ነው። በቃ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ጎንደሬ ነው። ጎንደር ህብረት ለፖለቲካ ስልጣን የሚሰራ ድርጅት ሳይሆን ከርስታቸው ተፈናቅለው ከትውልድ ቦታቸው የተባረሩትን ወገኖቻችን ወደቀያቸው ለመመለስ፤ እንደሰው ተከብረው እንዲኖሩ ለማድረግ፤ ከደረሰባቸው ውድቀት አገግመው ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ፤ በሃገራቸው እንዲጠቀሙ ፤ በማንነታችው እንዲኮሩ ለማድረግ ጎንደር ኅብረትን በማጠናከር ልንረዳቸው እንችላለን። ዛሬ የናቴ መቀነት ጠለፈኝ ብለን የምናመካኝበት ወቅት አይደለም። የተደራጀ ሃይል አለመኖር የጎንደርን ህዝብ ከአርባ አመት በላይ ለስቃይ እንደዳረገው በእድሜያችን አይተናል። የተለያዩ “የብሄርም” ሆነ የኅብረ ብሄር ፖለቲካ ድርጅት አባላት ልትሆኑ ትችላላችሁ። ያ መብታችሁ ነው የጎንደር ኅብረት አባል ከመሆንም አያግዳችሁም የሚፃረርም አይደለም። እንዲያውም እናንተ ድልድይ ሆናችሁ ድርጅታችሁ ከጎንደር ኅብረት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ማድረግ ትችላላችሁ።

ዛሬ “አገራችን ጎንደር ወንዛችን ተከዜ

ማነው የሚነካን እምብኝ ባልነ ጌዜ”

እያለ እንደ አያቶቹ ተከዜ ስር ለሚንጎራደደው ወገናችን ልንደርስለት ይገባል።

ስለዚህ ወገኖቼ ይህን እድል እና ድል ጊዜ ሳናባክን እንጠቀምበት፤ ብዙ ብዙ ልንሰራቸው የምንችላቸው ቁም ነገሮች አሉ። መዘግየት እንደገና ወደ ልመና ያቆመናል። ዛሬ ወደ ትውልድ ቦታው የገባው ሃይል በገባበት ሁሉ ተረጋግቶ መኖሩን እንዲቀጥል እንደ ቅኝ ተገዥ የኖረበት ዘመን አክትሞ እራሱን እያስተዳደረ በክብር እንዲኖር፤ ጎንደር ታሪካዊ ቦታዋን እንድትይዝ የግድ በመተባበር መስራት ይኖርብናል፤ ዛሬ ይህን ካደረግን በቀሪው ዘመናችን መንፈሳችን የሚያስደስት ለሕሊናችን ሰላም የሚሰጥ ስራ ከመስራታችን በላይ በታሪክ ከተጠያቂነት ነፃ እንሆናለን።

ተስፋሁን

Featured Posts
Recent Posts
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Classic
  • Twitter Classic
  • Google Classic
bottom of page