top of page

ፋኖነት፣ ኢትዮጵያዊነት


9/4/2023

ፋኖነት፣ ኢትዮጵያዊነት

የብልጽግና ምንነትና ማንነት እየጠራ መጥቶ ፓርቲው በፍጹም አክራሪዎች የሚመራ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ እንደሆነ አስመስክሯል። ትህነግ የተባለው ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አንድነት ሃይል አማራውን አጥፍቶ አራት ኪሎ ለመግባት ያደረገው ፋሺስታዊ ወረራ እንዴት በሽንፈት ተጠናቆ፣ ጅራቱን ቆልፎ አንገቱን ደፍቶ መቀሌው እንደተመለሰ የምናውቀው ነው። የፌደራል መከላከያ ሃይልም ከትህነግ ጥፋት እጁን ስቦ ያወጣው ሃይል ማን እንደሆን ያውቀዋል። ጉድብ ውስጥ አብሮ ውሎ እያደረ፣ ከፊት ተሰልፎ እየተዋደቀ፣ ቁስለኛ እያነሳና ስንቅ እያቀበለ የታደገው ፋኖና የአማራ ሕዝብ ነው። ትግራይ ውስጥ የተገደለው ተገድሎ፣ የተበተነው በጥማትና በረሃብ ተኮማትሮ እያነከሰ የአማራን ክልል ሲረግጥ እንዴት አይነት አንጀታዊ አቀባበል እንደተደረገለት ከሃዲ ይርሳው እንጅ ለእኛ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

የኦሮሞ ብልፅግናና ትህነግ የተፈራረሙት የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት ያለአማራው ተሳትፎ እያልን የጮህነው ዝም ብለን አልነበረም። በአማራው ላይ የተደረሰ ፀረ አማራ ስምምነት እንደነበርና በአሁኑ ወቅት የሚካሄደው ጦርነትም የዚያ ስምምነቱ ውጤት እንደሆነ ማንም አይስተውም። በአክራሪ ኦርሞዎች ተቀፍድዶ የተያዘው የብልፅግና ፓርቲ ሕግ ማስከበር በሚል ዘመቻ ድሮን እስከመጠቀም የደረሰ ጦርነት በአማራው ላይ በማካሄድ ላይ ነው። በዚህ አማራውን ኢላማ ባደረገ ጦርነት ሕዝቡን መግደል፣ ማሳደድ፣ ንብረቱን ማውደም ማፈናቀል የዚህ ፋሽስታዊ መንግሥት የቀን ተቀን ስራው ሆኗል። የሚገርመው ሌሎች ክልሎች በፍራቻ ተውጠው ዝም ማለታቸው ነው። ተላላኪዎች ተደማሪዎች እንበላቸውና በየክልሉ ብልፅግና ቢኖሩም እንደ የአማራው ብልፅግና ተላላኪዎች እርሙን የበላ የለም። በእኛ ስር ሆናችሁ እኛን መስላችሁ ከተደመራችሁ ፍርፋሪችን የናንተ ነው የተባሉ ጥቂት የአመራር አባሎች የገዛ ህዝባቸውን ለማስመታት ሲንቀዠቀዡ እያየን ነው።

ዛሬ ይህ የኦሮሞ ብልፅግና መንግሥት ከተቀዳበት የትህነግ ወንጀለኞች ጋር በመቀናጀት የአማራን ሕዝብ ትጥቅ አስፈታለሁ በማለት ያለ የሌለውን የመከላከያ ሃይል ወደ አማራው ክልል አዝምቷል። “እብድ ከወፈፌ ቤት ያድራል” እንዲሉ የሁለቱ ፀረ ኢትዮጵያ አክራሪዎች በአማራው ሕዝብ ላይ የከፈቱት ጦርነት ከ30 እና 40 ዓመታት በላይ ሲያካሂዱት ከቅዩት ፀረ አማራ ድርጊቶቻቸ የቀጠለ ነው። አሁን ለአንዴም ለሁሌም ቅስሙን ሰብረን፣ ያለቀው አልቆ የቀረው ተሸማቆ እንዲኖር እናደርገዋለን መሬቶቻቸውን ቀምተን ክልላችን እናስፋፋለን በሚል ቅዠት መቀበሪያቸውን እየቆፈሩ ነው። አበክረን የምንነግራቸው ቢኖር እስካሁን የኢትዮጵያን አንድነት የሕዝቦቿን መስተጋብር እንጠብቃለን በሚል አማራውና ኢትዮጵያ-ወዳድ ሁሉ ያሳዩት ትግስት እንደማይቀጥል ነው፡ “ሞኝን ሲታገሱት የፈሩት ይመስለዋል” እንዲሉ። በህልውናው ላይ ስትመጡ ግን ትግስቱ ተሟጦ ያልቃል፤ በወጉ ሳይደረጅ እንኳ ምን ማድረግ እንደሚችል አይታችሁታል። ማንም ሕዝብ በጦር ብዛት አይንበረከክም፤ አማራው ደግም የበለጠ ነው። በታሪኩ ለማንም ተንበርክኮ አያውቅም። ኢትዮጵያን የምትመስል እንጅ ሌላ ማንንም የምትመስል ኢትዮጵያ መፍጠርም አይቻልም፤ አትፈጥሩምም።

ፌደራል መንግሥቱ የማንነት ጥያቄ ባነሱት የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የራያ አካባቢዎች ውስጥ ከትህነግ ጋር ተቀናጅቶ የሚተበትበው ሴራ ሕዝባችን ደርሶበታል። ቄስ ና አስመሳይ ሽማግሌዎችን (አንዳንዴ የዋሆችን በማታለል) በመላክ፣ የትህነግ ወታደሮችን አሾልኮ ለማስገባት የሚያደርገውን ተንኮል ተነቅቷል። ይህን ለማድረግ የመከላከያ ዩኒፎርም ወደ ትህነግ መላኩን ሰምተናል። የትህነግ ወታደሮች ከመከላከያ ጎን እንደተሰለፉና በጥሮታና በግለላ የነበሩ መሪዎቻቸው፣ ሰላዮቻቸውና የጦር መሪዎቻቸው በፌደራሉ መንግሥቱ ውስጥ እየተሰገሰጉ እንደሆን ገብቶናል።። ትህነግና ፌደራል ነኝ የሚለው የኦሮሚያው ብልፅግና መንግሥት እጅና ጓንቲ ሆነው እየሰሩ እንደሆን ማንም አይስተውም። የእነሱ ተላላኪ የሆኑ ጥቂት የአማራ ብልፅግና አባሎችም ገንዘብ ተቀብለው በመርጨት ፋኖዎችን በማስከዳት አንዱን በሌላው ላይ ለማስነሳት ተልእኮ ተቀብለው እንደ እብድ ውሻ እየተንከለከሉ ነው። የአማራ ሕዝብ የፋኖ ጦሩን ይዞ እነዚህን ጣምራ ጠላቶቹንና ተላላኪዎቻቸውን ለሽንፈት ይዳርጋቸዋል። መላው የአማራ ሕዝብና ፋኖ እስካሁን ያደረገው ትግልና በነዚህ ጣምራ ጠላቶቹ ላይ የተቀዳጀው ድል አኩሪ ነው። ያሳየው ዲስፕሊን፣ ሰባዊነትና የሕዝብ ንብረት ጥበቃ ያውም መሪ ድርጅት በሌለበት ሁኔታ በጣም የሚያኮራና ዓለምን ያስደመመ ነው።

አማራው ይህን መንግሥት አምኖ የሚቀበልበት ሁኔታ ፈፅሞ የለም። ከ 5 አመት ታሪኩ ያገኘነው ሞት፣ ስደት፣ መዋከብ፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል ነው። ይህ መንግሥት የአማራ ጠላት ነው። ማንኛውንም አይነት ሽምግልና፣ ድርድር የሚል ማታለያ አማራው አይቀበልም።

መንግሥት በጎ ፍቃድ ማሳየት ከፈለገ፤

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አሁኑኑ መሳብ፤

ጦሩን ከወሰን አካባቢዎች በስተቀር ከአማራ ክልል ማስወጣት፤

መሳሪያ አስወርዳለሁ የሚል እቅዱን መሰረዝ፤

የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምትና የራያ ጥያቄ የፍትህና የማንነት ጥያቄ መሆኑን መንግሥት አምኖ ተቀብሎ፣ ሕዝበ ውሳኔ(ርፌረንደም) እና የፌደራል ግዛት ስር ክልል እያለ የሚዘላብደውን ማቆም፤

በእነዚህ አካባቢዎች ወንጀል ሰርተው ወደ ሱዳንና ወደ ትግራይ የሸሹ ወንጀለኖችን ለፍርድ ማቅረብ፤

በሌሎች ክልሎችና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን ፀረ አማራ ዘርፈ ብዙ ጭቆናና ማዋከብ ማቆምና የተፈናቀሉ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ማድረግ፤ አለበት።


ከዚህ አያይዘን በአማራ ብልፅግና ስም በተላላኪነት የሚያገልግሉ እራሳቸውን የበሉ ሆዳሞች ከተደማሪነት ተግባራቸው እንዲቆጠቡና ወደ ሕዝባቸው እንዲመለሱ እንመክራለን፤

የአማራው ትግል ያቸንፋል፣ ኢትዮጵያ ትፀናለች።



Featured Posts
Recent Posts
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Classic
  • Twitter Classic
  • Google Classic
bottom of page