top of page

በሰሞኑ በቅማንትና በአማራ ማህበረ ሰቦች መካከል ስለተፈጠረው ግጭት ከጎንደር ህብረት የተሰጠ መግለጫ


ጥር 11, 2019 ዓ. ም.

በሰሞኑ በቅማንትና በአማራ ማህበረ ሰቦች መካከል ስለተፈጠረው ግጭት ከጎንደር ህብረት የተሰጠ መግለጫ

በሰሞኑ በመሃከልና በምእራብ ጎንደር የደረሰው የብዙ ዜጋዎች መሞት፣ መፈናቀልና የንብረት መውደም በጣም አሳዝኖናል፤ ልባችንንም ሰብሮታል። በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት አንድ የሆኑ፣ ተጋብተውና ተጎራብተው አንድ ስነልቦና አንግበው በክፉም ሆን በደጉ ጊዜ ሳይለያዩ የኖሩ ወንድማማች ማህበረ ሰቦችን ሲዳሙ እያየን ነው። ለዚህ ሁሉ ጥፋት መነሻ የሆነው ህዝብ በቅጡ ሳይመክርበትና ድምፁን ሳይሰጥበት በተለያዩ እናውቅልሃለን በሚሉ እጆች የወደቀው የክልል ጉዳይ ነው። ዛሬ፣ ብጥብጥ በበሰፈነባቸው አካባቢ የሚኖሩ ወንድማማች የቅማንትና የአማራ ማህበረሰቦች የሚሰሙት የእነዚህ አበጣባጭ ድምፅ ብቻ ነው። መጣብህ ተዘጋጅ! በለው! ተወረርክ! አትምጡብን! ውጡልን! የሚለው ድምጽ ብቻ ነው የሚያስተጋባው። በማህበረ ሰቦቹ ውስጥ ያሉ የአገር ሽማግሌዎች ድምፃቸው ተቀብሯል። የሃይማኖት አባቶች ሰሚ አጥተዋል። መንግሥት መኖሩ አይታወቅም። የሩቅ ተመልካች ሆኗል። በታሪካችን እንደሚታወቀው መንግሥት በሌለበት ሁኔታ እንኳ እራሱን በራሱ በማስተዳደር የሚታወቀው ህዝባችን ዛሬ ግራ ተጋብቷል።

የጎንደር ህብረት ይህ ሁኔታ እንዳይደርስ ላለፉት አራት ዓመታት ሲታገል ቆይቷል። ጥር 10 2019 ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ይህን ችግር ለመፍታት በመጀመሪያ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ወስዶ አካባቢውን ተቆጣጥሮ ፀጥታውን ማስጠበቅ አለበት። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምንም ማድረግ አይቻልም። ዴሞክራሲ፣ ውይይት ልማት፣ ሽምግልና እያሉ ቢያወሩት መተግበር ቀርቶ መናገር እንኳ አይቻልም። ለዚህ ሁሉ ቀውስና ግራ መጋባት የክልሉ መንግሥት የሚያስተዳድራቸውን ግዛቶች እንኳ መቆጣጠር አለመቻሉ ነው። ‘መጀምሪያ መቀመጫየን አለች ዝንጀሮ’ እንደሚባለው መጀመሪያ ሰላም ማግኘትና ጸጥታውን ማስከበር ነው። ይህ ቀውስ የሚሊሺያ ጦር ከመጠቀም ያለፈ ነው። ሚሊሺያ በሚል ስም ህዝብን በህዝብ ላይ ማዝመት ደግሞ ቀውሱን ማባባስ ነው። ይህንም እያየን ነው። በሌላው በኩል ወንጀሎኝችን ህዝብ አስሮ ሲሰጥ ሳያጣሩ መፍታት በምንግሥት ላይ ያለውን እንጥፍጣፊ እምነት ጨርሶ ማጥፋት ነው። ይህንም ታዝበናል። የማያወላውል እርምጃ ወስዶ ሰላም ለማስፈን መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ መውሰድ አለበት። ወደሰላማዊ ኑሮ መመለስ ለሚፈልጉት የምህረት እድል ሊሰጥ ይገባል። ብረት አንግበው በህዝቡ ላይ ሰቆቃ እየፈፀሙ መቀጠል የሚፈልጉትን ደግሞ ማንበርከክ አለበት። አዋጅ አውጆ፣ አለሁ ብሎ ለህዝቡ ድምፁን ማሰማት አለበት።

ህዝቡ ፀጥታው ተጠብቆ፣ አቅሉ ተመልሶ፣ ሰላሙን አግኝቶ፣ እራሱን አሰባስቦ በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበትና እንዲወያይበት ጊዜ ሊያገኝ ይገባዋል። የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን ከሁለቱ ማህበረሰቦች ጋር ምክክር እንዲያደርጉና መፍትሄ እንዲያፈላልጉ እድል ማግኘት የግድ ነው። መንግሥት ይህ እንዲሆን አስፈላጊውን እርዳታ ሁሉ ማድረግ አለበት። በተለይም ከስጋት ነፃ በሆነ መንገድ ስራቸውን እንዲሰሩ ማረጋገጫ ሊሰጥ ይገባዋል።

ከላይ የተዘረዘሩት እየተፈፀሙ ባለበት ጊዜ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ ከስራ ገበታቸው የተባረሩ ሁሉ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ፣ ተማሪዎች ወደየትምህርት ቤታቸው ተመልሰው እንዲገቡ፣ ንብረታቸው የወደመባቸው እንዲቋቋሙ በሚደረገው ጥረት መንግሥት ያንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ ይጠበቅበታል።

የሁለቱ ማህበረሰቦች በቂ የማገገምያና የውይይት ጊዜ ከተሰጣቸው በኋላ ከማንም ተፅእኖ ነፃ በሆነ መንግሥት በክልል ላይ ሬፈረንደም ቢወሰድ ተገቢ ነው እንላለን። ይህን ስንል እነዚህ አንድ ሆነው ሳል ሁለት የምንላቸው በሰከነ አእምሮ አንድነታቸውን እንደሚመርጡ ተስፋ በማድረግ ነው።

ቅማንት አማራ ተብለን በመጠራታችን ሁለት ማህበረሰቦች እንላለን እንጅ ሁለት የሚያስብለን ምንድን አለ?? የጎንደር ህብረት በፅኑ የሚያሳስባችሁ አንድ አርጎ ያቆየን ጎንደሬነታችንና ኢትዮጵያዊነታችን ጠብቀን በአንድነታችን የምናገኘውን ድል በምንም መንገድ ቢሆን ተነጣጥለን ልናገኘው አንችልምና በእጃችሁ የቆየውን ወርቅ፣ አንድነታችሁን እንዳታጡ አጥብቀን እንማጸናችኋለን። በአንድ ቤት ሲኖር ወንድማማችም ይጣላል፤ ይህ ያለ ነው፤ ለመጠፋፋት ሲሆን ግን እብደት ነው። ደግመን፣ ደጋግመን የምናሳስባችሁ የቆየውን የጋራ እሴቶቻችሁን ጠብቃችሁ አንድነታችሁን እንድታጸኑና ወደኋላ የቀረውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ተባብረን እንድንገነባ ነው።

Featured Posts
Recent Posts
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Classic
  • Twitter Classic
  • Google Classic
bottom of page