የንፁኀን ጀግኖች ወገኖቻችን ደም ለኢትዮጵያ ሐውልት ነው።
6/25/2019
የንፁኀን ጀግኖች ወገኖቻችን ደም ለኢትዮጵያ ሐውልት ነው።
ባሳልፍነው ሳምንት መጨረሻ በሐገራችን አቆጣጠር ሰኔ 22 2011 በአማራ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ ባህርዳር እና በአዲስ አበባ የተፈፀመው ለማመን የሚከብድ አስቀያሚ፤አሰቃቂና ከሰባዓዊ ርህራሄ ውጭ የሆነ ተግባር እንደ ሰውም ሆነ እንደ ዜጋ እጅግ ልብ የሚያደማ ታሪክ ይቅር የማይለው ተግባር መፈፀሙ የጎንደር ህብረትን እጅግ አሳዝኖል።
የተሞከረው የረቀቀ ተንኮል ሁለት ሰይፍ ይዞ አንድነታችንን ሊያፈራርስ እንደነበረ ተረድተናል። ይሁን እንጅ የተፈፀመው እኩይ ተግባር የዚህ አሳፋሪና አሳዛኝ ሴራ ጠንሳሽ ለሆኑት አካላት አንገት የሚያስደፋ፣የሚያሸማቅቃቸው እንጅ የሚያኮራቸው አይደለም።ይህ አደጋ ለመላው ሀገራችን የሚያስከትለው ችግር ከባድ ነበር።
ቢሆንም “ሚስማር ሲመታ ይጠብቃል” እንዲሉ አገራችን በቀደመ ታሪኳ ያጋጠሟትን የአንድነትና የነፃነት አደጋዎች በቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት በዜጎቿ አይበገሬነትና አንድነት እንደ ሚስማር እየተቀጠቀጡ ህያው ታሪካችንን እንዳስረከቡን ሁሉ አሁንም ይህን ፈተና በተመሳሳይ ሁኔታ እንደምተወጣ አንጠራጠርም።
ይህ ይሆን ዘንድ አገራችንም የጀመረችውን የለውጥ ሂደት ዳር ለማድረስ ሲባል ህዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ትግሉን መቀጠሉ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን።
በይበልጥ ደግሞ በአሁኑ ስዓት የዚህ አሳፋሪ ተግባር ሰለባ የሆነው የዐማራው ክልል ህዝብ በተፈፀመው ነገር አንገቱን ሳይደፋ፤ጉዳዩ የጥቂት መሰሪዎች መሆኑን አምኖ የተፈጠረውን አሳዛኝ ክስተት ለመልካም በመለወጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላምና በፍቅር የኖረበተን ታሪክ ለማስቀጠል በተረጋጋ ሁኔታ ኃላፊነቱን እንዲወጣና እርስ በርሱ እንዲተባበር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የዐማራ ክልል ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለሐገራችን የከፈለው መስዋዓትነት በእንዲህ አይነት ውዥንብር ሲበከል የማይቆጨው ይኖራል ብለን አናምንም። በሰከነ መልክ አንድነቱን ጠብቆ የተጋረጠበትን ከባድ ፈተና በፅናት ለማልፍ ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርግ ስናሳስብ በአንፃሩ ይህንን ክፍተት በመጠቀም የአማራ ክልል ወገናችንን አንድነት ለመቦርቦር፣አንገቱን ለማስደፋት፣ሌት ተቀን ለምትባዝኑ ቡድኖችም ሆናችሁ ግለሰቦች ከዚህ ክፋፋይ ተግባራችሁ እንድትቆጠቡ የጎንድር ህብረት በፅኑ ያሳስባል።
በመሆኑም፤ጥፋትን በጥፋት በመመለስ የምናመጣው ጥሩ ታሪክ ባለመኖሩ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ለከፋ ጥፋት የሚዘጋጁ ካሉ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይከፋፍል አካባቢውን እንዲጠብቅ አንድነቱንም ከሚቦረቡሩ እኩዮች እራሱን እንዲከላከል አደራችን የጠበቀ ነው።
ለዐማራ ክልል መንግስት
የህዝባችንን ሰላምና አንድነትን ለመጠበቅ በአስቸኳይ ከሀይማኖት መሪዎች; ከሀገር ሽማግሌዎች; ከወጣቶች ከሙህራንና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመተባበር የማረጋጋት ስራ እንዲሰራ እንጠይቃለን።
ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት
በባህርዳርና በአዲስ አበባ ለተፈፀመው ግድያ አንድ ከህዝብ የተወጣጣ በዐማራ ህዝብ ተቀባይነት ያለው የምርመራ ኮሚሽን ተቋቁሞ በአስቸኳይ የምርመራና የማጣራት ስራውን እንዲስራና ግኝቱን ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ስናሳስብ የፌደራል መከላከያ ሀይል በአማራ ክልል ውስጥ ህግን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ሳናመሰግን ባናልፍም በመላው ሀገሪቱ ውስጥ በአዋጅ የፀደቀና የተተገበረ የትጥቅ ማስፈታት ህግ ሳይኖር በዐማራ ክልል ውስጥ ትጥቅን ለማስፈታት የሚደረግ ጥረት እንዳይኖር በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳልን።
በመጨረሻም ለህዝባቸውና ለሐገራቸው በቃልኪዳን ቆመው ለተሰውት ሁሉ እግዚአብሔር ነብሳቸውን በአፀደ ህይዎት ያኑርልን።
እንዲሁም፤ለቤተሰቦቻቸውና ጎደኞቻቸው መፅናናትን እንመኛለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ታፍራን ተከብራ ትኖራለች።
የጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት።