top of page

‘ሊጣላ የመጣ፣ ሰበብ አያጣ’

መጋቢት 23 2012 (04/01/2020) ‘ሊጣላ የመጣ፣ ሰበብ አያጣ’ በሰሞኑ በጎንደርና በዙሪያዋ ተከታትለው እየደረሱ ያሉ አጠያያቂ ጉዳዮች የፌደራሉ፣ የክልሉንና ሌላንም ክልል ያካተተ ጉዳይ በሚመስል ሁኔታ እየተካሄዱ ናቸው። እንደሚታወቀው በጎንደርና በዙሪያዋ ሆነው የማያውቁ፣ ከታሪኩና ከባህሉ የራቁ ወንጀሎች በገጠርና በከተማዎች እንደተፈጸሙ ግልጽ ነው። ሕዝቡም የመንግሥት ያለህ እያለ ሲጮህ መቆየቱ የሚካድ አይደለም። መንግሥትም በተለይም የክልሉ መንግሥት በአቅም ማጣትም ይሁን ባለመፈለግ ጀሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሲያደናቁር ቆይቷል። መቸም በአገራችን አሁን የመጣብን ጉድ ሌላ ነው። መንግሥትና የሕግ የበላይነት፣ መንግሥትና ሰላም ማስከበር ከፊት መዟዟር አልፈው በመጠላለፍ ላይ ናቸው። ወንጀለኛ የማይጠየቅበት፣ ተይዞ ለፍርድ ማይቀርብበት፣ ወይንም ተፈርዶበት ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ የሚፈታበት፣ ተከሶ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የሚለቀቅበት ጊዜ መጥቶብናል። በዚህ ላይ ነገን የሚሰጉ ባለስልጣናት በመንግሥት መዋቅር ተሰግስገው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሁኔታውን እያባባሱ ቀውሱን እያጦዙት ነው። የህዝብ ጥያቄዎች ገብያ ወጥተው የፖለቲካ ቡድኖች ጥቅም ማወራረጃ እየሆነ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሸከመው ቀንበር ምንኛ ከባድ ነው!! ከሁለት ዓመት በፊት ለተገኘው ለውጥ ትልቅ ኃይል የነበረው የጎንደር ሕዝብ የዚህ መከራ ገፈታ ቀማሽ ብቻ ሳይሆን፣ ቅስሙን ለመስበር ያልተቋረጠ ደባ እየተጎነጎነበት ነው። የክልሉ መንግሥት ሰላም ማስጠበቅ አቅቶት፣ ሰላም ለማስጠበቅ ዝግጁ ሕዝብ ቢኖረውም እንኳ ለማስተባበርና የመንግሥት ሚናውን ለመጫወት ባለመቻሉ ስርአት አልበኝነት ከተማዋንና አካባቢዋን አናውጧል። አፋኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ዘራፊዎችና በረት ሰባሪዎች ብዙ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ተመልክተናል። ሕዝብ ይዞ የሰጣቸው ለፍርድ ሳይቀርቡ ይለቀቃሉ፣ የተፈረደባቸው ተፈተው ወደ ወንጀል ስራቸው ይመለሳሉ። ባለፉት ሁለት ዓመታት ሕዝብን ግራ ያጋባ ሁኔታ ሆኖ ቆይቷል። ወንጀለኛ ሌላ ስም የለውም፤ ወንጀለኛ ነው። የመንግሥት ሰራተኛ ይሁን ፋኖ፣ የሌላም የሌላም ድርጅት አባል ይሁን፣ ሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማራ ሁሉ ወንጀለኛ ነው። ወንጀለኛን በሕጋዊ መንገድ ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው። ባለፈው ሳምንት በዳባት አካባቢ በተነሳው ግጭት ምክንያት ጎንደር የታቃውሞ ሰልፍ ተደርጎ ከ2 እስከ 4 የሚሆኑ ሰዎች በጥይት ቆስለዋል። ይህን ተከትሎ አዘዞ የነበረው 33ኛ ሻለቃ በጎንደር ከተማ የፋኖ ካምፕ አለባቸው የተባሉ በሁለት ቀበሌዎች በሌሊት ደርሶ ከባድ መሳሪያዎችን በጨመረ ጦርነት በመሰለ ተኩስ ከተማዋን ሲንጣት አድርዋል። እነዚህ ካምፕ የተባሉ ቤቶች እስካሁን እንዴት እንደ ካምፕ ሊኖሩ እንደቻሉ ክልሉ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። ፋኖ የሚለው ቃል በታሪካችን እንደምናውቀው የእድሜ ክልል ወይንም የሙያ መስክ ወሰን የለውም። ደሞዝተኛም አይደለም። በችግር ወቅት ተነስ ተባለም አልተባለም በራሱ ሰንቆ ለአገሩ ሕይወቱን የሚሰጥ ነው። ማንም ወንጀለኛ ተነስቶ ፋኖ ነኝ ብሎ በፋኖ ስም መጠቀም ሌላ ተጨማሪ ወንጀል ነው። መንግሥትም ማንንም ወንጀለኛ የፋኖ ስም ሰጥቶ ሃቀኛ አገር ወዳዶችን ማሳደድ የለበትም። ሰላሙን ለማስጠበቅና ሕግ ለማስከበር መንግሥት በራሱ ሕዝብ ላይ በደረቅ ሌሊት ሄዶ የጥይት ዝናብ ማዝነብ አያስፈልገውም። ሻለቃ ጦር ማዝመትም አልነበረበትም። ምንም እንኳ በወንጀለኛዎች ላይ የተደረገውንም ሆነ የሚደረገውን ስርአት የማስከበር እንቅስቃሴ ብንደግፍም፣ አሁን የምናስተውለው የፌደራሉና የክልሉ መንግሥታት እንቅስቃሴዎች በጎንደር ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩና እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ሂደቶች መሆናቸውን ነው። በቀውስ እየተናጠ የቆየው የአማራ ክልል ከቀውስ ወደ ቀውስ እየተሽመደመደ ደመ ነፍሱን የሚጓዝ ክልል ነው። 27 ዓመታት በወያኔ ተላላኪዎች ተሞልቶ ወያኔን ሲያገለግል የኖረ እንደነበር ማንም የሚያውቀው ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሌሎች የተካሄደውን ያህል ለውጥ በዚህ ክልል ውስጥ አልተካሄደም። ስለሆነም ብዙ የወያኔ ቅሪቶች አሁንም በመካከሉ ተሰግስገው ጸረ ሕዝብ አጀንዳቸውን እያራመዱ ነው። አንጻራዊ ለውጥ መጣ ከተባለም በኋላ የውጭ እጅ የበዛበት ክልል ቢኖር የአማራ ክልል ብቻ ነው። እነዚህ የውጭ ሃይሎች ክልሉን ደካማ አድርገው ለማቆየት ያላደረጉትና የማያደርጉት የለም። የሰኔ 15ቱ የእነ ዶ/ር አምባቸው ግድያም የዚሁ ሂደት መገለጫ ነው። ከዚያም በኋላ ይህን ስበብ አድርገው ወንጀለኞችን ትተው በወንጀሉ የሌሉበትን ተቆርቋሪዎች ማሰርና መወንጀል ነው የተያያዙት። ይህን ያህል ወንጀል ተፈጽሞ የተፈረደበትም የለ። ከማሰርና መፍታት ሌላ የታየ ነገር የለም። ለሕዝብም ይፋ የተደረገ ነገር የለም። ዛሬ፣ ፍትህ የሚለው ቃል እራሱ ሊጠፋብን ነው። አቅደው እንዳይሰሩ የክልሉ ሹማምንት እንደ መኪና ዘይት በወራት ይቀየራሉ። ክልሉ እንዳይረጋጋና እንዳይጠናከር የሚደረግ ያላሰለሰ ጥረት እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል። አሁን በጎንደር የተፈጠረው ሁኔታ የዚሁ ሂደት ቅጥያ ነው። በፖሊስ ሊያዙ የሚችሉ ወንጀለኞችን ለመያዝ በሌሊት ሻለቃ ጦር ልኮ ኦፐሬሽን ማካሄድ፣ ጦር በፌደራል ደረጃ ወደ አካባቢው ከተለያየ አቅጣጫ ማንቀሳቀስና፣ ወያኔ ጦሩን ወደ ጎንደር ማስጠጋት ባጋጣሚ ነው ብለን ለመቀበል ያስቸግረናል። የሕዝቡን ትግል ለማፈንና ከወያኔ ጋር የፖለቲካ ማወራረጃ ለማድረግ የታቀደ እንቅስቃሴ ይሆን? የሚል ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባል። በተለይ ደግሞ አለምን ያሸበረው የኮረና ቫይረስን ለመከላከል ሕዝብ በጭንቀት ላይ ባለበት ሁኔታ በኢኮኖሚና በሶሺያል ችግር በደቀቀው ጎንደር ላይ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ ማካሄድ አይነተኛ የማጥፋት ቀመር ከመሆን አይዘልም። ሁኔታውን ለማቀዝቀዝና ብሎም መፍትሄ ለመስጠት የሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች፣ የወጣት ተወካዮችና የፋኖ አባሎች ነገሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያቀረቡት ጥያቄ ተሰሚነት ማጣቱ ግራ የሚያጋባ ተጨማሪ ምክንያት ነው። መከላከያ የዚህ ውይይት ክፍል መሆኑ ለምን ይሆን? ባይስማማስ? ይህ የወሳኝነት ሚና በፌደራሉ ደረጃ የተሰጣቸው መመሪያ ከሆነ የበለጠ ጥርጣሬያችን ያጠናክረዋል። እንዲያውም ፌደራሉ ያለ ክልሉ ፈቃድ መግባት አይችልም፤ ክልሉም ፌደራሉን የሚጠራው አቅም ሲያጥረው ብቻ ነው። እሁን ክልሉ እያለን ያለው ወንጀለኛ ይዤ ማሰር አቃተኝ ነው ? መቸ ነው ሞክሮ ያቃተው? እና ለዚህ የፌደራሉን እርዳታ ጠራ!? ወደ ጎንደር የሚያመሩ የመከላከያ እንቅስቃሴዎች በማን ጥያቄ ነው? በዚህ ሳብያ ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ለምን አስፈለገ? ክልሉን ለማሽመድመድ? የጎንደርን ሕዝብ ቅስም ለመስበር? የፌደራሉን አካሄድ ስንገመግም ‘ሊጣላ የመጣ ሰበብ አያጣ’ እንዲሚባለው የአባቶች አነጋገር ሆኖ አግኝተነዋል። አሁንም አኛ የምናሳስበው፤ 1ኛ/ አዋጅ መሰል መግለጫዎች ታጥፈው፣ በምትኩ የክልሉን ችግሮች ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፋኖ ተወካዮች፣ ከወጣቶችና ከምሁራን ጋር ክልሉ በውይይት እንዲፊታው። ጎሕም የዚህ መፍትሄ አካል ለመሆን ያለውን ፈቃደኝነት በዚህ አጋጣሚ መግለጽ ይወዳል። 2ኛ/ ወንጀለኛ የሆነ ሁሉ ሌላ ስም ሳይፈለግለት በሕጋዊ መንገድ ለፍርድ ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ። ፍርዱም ተፈጻሚነት እንዲኖረው። ይህ መሆን ሲገባው ለዛሬው አንጻራዊ ነጻነት ያበቁን፣ እንደ አርበኛ መሳፍንት እና አርበኛ አረጋ ባሉ ሰርቶ አደር አርበኞቻችን ላይ አፈ ሙዝ ማዞር ከካህዲነት ተግባር አይወጣምና በተሎ እንዲቆም። 3ኛ/ በጎንደርና በዙሪያዋ ፌደራሉና የወያኔ ጦሮች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያቆሙና ሕዝቡን ከማሸበር እንዲቆጠቡ። ክልሉ ይህን እንዲጠይቅና የራሱን ችግር በእራሱ እንዲፈታ። በክልሉ ላይ ያለውን ሥልጣንና መብት እንዲያስከብር እንጅ ‘ፈሪ በራሱ ጠብ ገላጋይ ይሆናል’ እንደሚባለው በራሱ ጉዳይ ገላጋይ መስሎ መቅረቡን እንዲያቆም። 4ኛ/ ክልሉና የፌደራሉ መንግሥታት በአሁኑ ጊዜ አቅማቸውን በሙሉ የኮረና ቫይረስ መከላከል ላይ እንዲያውሉና በሕዝቡ የደህንነት ጥያቄ ላይ እንዲያተኩሩ። 5ኛ/ ክልሉ በልማት ረገድ ወደ ረሳቸው የጎንደር ዞኖች ፊቱን እንዲመልስና እንደሌሎቹ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ቀጠና እንዲያቋቁም፤ እያልን አሁን በመካሄድ ላይ ያለው የአማራውን ክልል የማዳከምና የጎንደርን ሕዝብ የማሸበር የሴራ እንቅስቅሴ እንዲቆም እንጠይቃለን። አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች !!!

Featured Posts
Recent Posts
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Classic
  • Twitter Classic
  • Google Classic
bottom of page