ጎንደር ሕብረት 1.5 ሚሊዮን
- Abebe Gelagay
- Apr 14, 2020
- 1 min read
የጎንደር ሕብረት የኮረና ቫይረስን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አንድ ሚሊዮን ተኩል የኢትዮጵያ ብር መደበ እንደምታውቁት የኮረና ቫይረስ ሁሉንም አገራት እያዳረሰ ነው። ባገራችን መግባቱን የማያውቅ አለ ብለን አናምንም። ባህላችንም ሆነ ጥብቅ የእምነት ስነስርአቶቻችን ለበሽታው መዛመት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። በዚህ ላይ አብዛኛው ሕዝብ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነው። አንዳንዴም በቀን አንድ ማእድ ለማግኘት እንኳ የሚሳነው ሕዝብ ብዙ ስለሆነ እንዴት ሊሆን ነው ብሎ ማሰቡ ብቻ ሰቀቀን ውስጥ ይከታል። ይህን ትልቅ መቅሰፍት ለመከላከል የሕዝቡ አቅም ውሱን ነው። ስለሆነም በብዙ መንገድ ከሕዝባችን በተሻለ ሁኔታ ላይ የምንገኝ የቁርጥ ቀን ወገኖቹ የቻልነውን ያህል በመርዳት ሕይወት ማትረፍ የውዴታ ግዴታችን ነው። ጎንደር ሕብረት በጎንደር ክፍለ ሃገር አካባቢዎች በተቋሞች መዘጋትና ተለይቶ በቤት ውስጥ በመዘጋት ምክንያት የሚደርሱ ችግሮችን ለመቀረፍ ከበጎ አድራጊዎች እርዳታ በማሰባሰብ ላይ ነው። ጎሕ የኮረና ቫይረስን ለመከላለል ለምግብ እርዳት የሚሆን አንድ ሚሊዮን ተኩል (1 1/2 ሚሊዮን) ብር መድቧል። የችግሩን መጠን በመረዳት፣ ተከታታይ እርዳታዎችን ለማድረግ የገንዘብ ማሰባሰቡ እንዲቀጥል ወስኗል። ችግሩ ጊዜ አይሰጥምና እርዳታው በአስቸኳይ እንዲደርስ ጎንደር ላለው ቅርንጫፍ መመሪያ ያስተላለፈ ሲሆን፣ መሬት ላይ ባለው ዘገባ ላይ ተመስርቶ እንደሁኔታው የእርዳታውን መጠንም ከፍ ለማደርግ ወስኗል። ጎንደር ያለው የጎሕ ቅርንጫ ኮሚቴ በየዞኑ ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች ጋር በመተባበር በጎንደር፣ በደብረታቦር፣ በዳባትና በግንድወሀ ማእከሎች ሆኖ እርዳታውን እንዲያደርስ መመሪያ አስተላልፏል። ወደፊት ተጨማሪ እርዳታዎችን ለማድረስ ጎሕ ጥረቱን ይቀጥላል። እርዳታችን ከፍ ማድረግ የምንችለው አባላትና ደጋፊዎቻችን ስትረዱንና ስትረባረቡ ስለሆነ ትብብራችሁን አጥብቀን እንጠይቃለን። ችግራችንን በሕብረት እንወጣዋለን። የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት
Comments