‘በተለሙ ያርሷል፣ በጀመሩት ይጨርሷል፤’
በተለያዩ ውጥረቶች ውስጥ የኖረችው ጎንደር ለየት ያለ ዜና ይዛ ተሰምታለች። ሁሉም እንደሚያውቀው ከውጥረት ወደ ውጥረት ስትረማመድና የመሻኮችያ፣ የሴራ፣ የቀውስ መናሃሪያ ሆኖ ቆይታለች። ይህ ብቻ አይደለም የእነ አይበገሬ አገርም ሆና ስትታገል ኖራለች። በቅርቡም ያ የተለመደው ቀውስ ተከስቶባት በ የካቲትና በመጋቢት ቀውሱን አስመልክቶ መግለጫዎችን ማውጣታችን የሚታወስ ነው። ባወጣናቸው መግለጫዎች ሰላም የሚገኘውና ዴሞክራሲ የሚሰፍነው የህዝብ ተሳትፎ ያለበት ውይይት ሲካሄድ ብቻ እንደሆን አመላክተን ነበር። ባለፉት ቀናት ለሳምንታት በመንግሥት፣ በሚሊሺያ/ፋኖ ወኪሎች በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት መሪዎች መካከል ሲካሄድ የቆየው ውይይት በሰላም በስምምነት ተቋጭቶ መስማታችን በጣም ደስ ብሎናል። ተሳታፊ የነበሩትን የመንግሥት ባለስልጣኖች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና የሚሊሺያ/የፋኖ አባሎች እንኳን ደስ ያላችሁ እንላለን።
ይህን የተስፋ ጭላንጭል ማየታችን ደስ ቢለንም ወደፊት ለሰላም የሚደረገው ጉዞ ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ ስጋታችን መግለጽ እንገደዳለን። አካባቢው ላይ የሚራኮቱት ሃይሎች ብዙ ናቸው። እጃቸውም እረዥም ነው። ይህን የእርቅና የአንድነት ጥንስስ ‘ይኸኔ በእንጭጩ’ እንደሚሉ አንጠራጠርም። ለዚህ አይነተኛ መፍትሄው የክልሉ መንግስት እና ሕዝቡ የውስጥ ሰላምና አንድነት ሲኖራቸው ብቻ ነው። እሩቅ መሄድ አያስፈልግም። ስምምነቱ በተደረገ በነጋታው በአንድ በእርቁ ሂደት ላይ በነበረ የፋኖ አባል ላይ የተፈጸመው ግድያ ስምምነቱን ለማፍረስና የሰላም ሂደቱን ለማደናቀፍ የተደረገ ሙከራ እንጅ ሌላ ምክንያት አይኖረውም። በዚህ ግድያ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆንና ስምምነቱ እንዳይፈርስ በስምምነቱ ተሳታፊዎች የተደረገው ጥንቃቄና የታየው ትእግስት ሌላ የብስለት ስራ ነው እንላለን።
ይህ በዳባት ዙርያ የታየው የሽምግልናና የእርቅ ስራ በሌሎችም የጎንደር ዞኖች በፍጥነት መካሄድ ይኖርበታል። ሳይቀድሙን እንቅደማቸው የሚሉ ተንኮል ሰንቀው የሚዘዋወሩ እንዳሉ መዘንጋት የለብንም። ጸጥታውን ለማደፍረስ ወደ ነበርንበት የሽብር ሁኔታ እንድንገባ፣ ሳይመሽብን ማለታቸው አይቀርም። ተራ ወንጀለኞችን በተለያየ ስም መምጣታቸውም አይቅሬ ነው። በቅርቡ ገንዳ ወሀ አካባቢ ወንበዴዎች መኪና አስቁመው ሰላማዊ ሰዎችን ማገታቸው ይህን ያሳየናል። ለዚህ መፍትሄው ከሕዝብ ጋር የተባበረ ክንድ ማሳየት ነው። ዛሬም ሆን ነገ ሕዝቡ የሚጠይቀው ሰላምና ጸጥታ ነው። ለዚህም አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ሕዝብ ነው። “ማን ያውቃል አገር ማን ያጠብቃል ማገር” እንዲሉ ከሕዝብ ጋር የመከረና ሕዝብን የያዘ አቸናፊ እንደሚሆን አንጠራጠርም።
ሌላው ደግሞ ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ አይቶ የማያውቀው የጎንደር ሕዝብ ሰላሙን ካገኘ በኋላ ፊቱን ወደ ልማት ለማዞር ያለውን ጠንካራ ፍላጎት እንድታውቁለት ነው። እስካሁን በታዩት መንግሥታት ሁሉ በልማት ረገድ የተረሳው የጎንደር ሕዝብ በሆዱ ያነገበው ቅሬታ ሰፊ ነው። የልብ ትርታ ማዳመጥ ድረስ አያስኬድም፣ ለሚያዳምጥ በግልጽ በየትም ቦታ የሚነገር ነው። የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግሥታት የጎንደር ሕዝብ በልማት ረገድ የሚገባውንና ድርሻውን ሊያደርጉለት ይገባል። ለረዥም ጊዜ በተለያዩ ቀውሶች ሲናጥ የቆየው የጎንደር ሕዝብ ክልሉንም ሆነ ፌደራሉን በርቀት በጥርጣሬና በትዝብት እያያቸው እንደሆን መረዳት አለባቸው።
ለማንኛውም በሰሞኑ በመንግሥት አካሎች፣ በሚሊሺያ/ፋኖዎችና በአገር ሽማግሌዎች የተከናወነው የእርቅ ተግባር ደስ የሚያሰኝና ተስፋ የሚሰጥ ነው። ሂደቱ በግለት ይቀጥል እንላለን።
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኑር፤
የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት