በምርጫ ስም በወልቃይትና በራያ...
- Abebe Gelagay
- Sep 5, 2020
- 2 min read
ነሐሴ 28 2012 (9/4/2020)
ህወሓት፣ በምርጫ ስም በወልቃይትና በራያ ሕዝብ ላይ ዘምቷል
ደጋግመን እንደገለጽነው በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ሆኖ የማያውቀው የዘር መካለል ህወሓት ካመጣብን ወዲህ በሕዝቦች መካከል መቃቃር መገፋፋት፣ ስደት እልቂት መፈናቀል የታሪካችን አንድ ገጽ ሆኗል። ወያኔ ታላቋ ትግራይን ለመፍጠር ባለው ቅዠት የወልቃይትን፣ ጠገዴን ጠለምትንና ራያን በጦርነት በመዋጥ ወደ ትግራይ ከጠቀለለ ቆይቷል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች በግዴታ ትግራይነትን አንቀበልም በማለታቸው በጅምላ ተፈጅተዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል። ታስረው በመሰቃየት ላይ የሚገኙትን የትግራይ እስር ቤቶች ይቁጠሩት። ምን ይህል ስቃይ እየተቀበሉ እንደሆን አንዳንድ ከእስር ያመለጡ የሚናገሩትን ያልሰማ አለን ብለን አናምንም። በመሬቱ ላይ የሚገኙት በቋንቋቸው በአማርኛ እንዳይናገሩ ተከልክለዋል። ወደ አማራ አካባቢ እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል። አያት ቅድመ አያቶቻቸው በኖሩበት ተወልድው ባደጉበት አንገታቸውን ደፍተው እ

ንዲኖሩ ተገደዋል። ትግሬነታችሁን ካልታቀበላችሁ ውጡ እየተባሉ ነው።
ጠባቡና እብሪተኛው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከተጣላ ሁለት ዓመታት አልፈውታል። ዛሬ ብቸኛው አፈንጋጭ ወያኔ ሲያሰኘው ኑልኝ ልግጠማችሁ ብሎ ይፎክራል። ሌላ ጊዜ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ልትወረር ነው! ከእኔ ጋር ከተሰለፍክ ብቻ ነው መዳን የምትችለው እያለ የፍራቻ ቅዠት ይቃዣል። በሙስና የተዘፈዘፉና በጸረ ኢትዮጵያነታቸው የታወቁ የህወሓት አመራሮች መቀሌ ላይ ከትመው የትግራይን ሕዝብ በማስፈራራትና በውሸት ፕሮፖጋንዳ ምሽግ ለማድረግ እየጣሩ ነው። የፌዴረሽኑ ምክር ቤት ስብሰባ ቢጠራቸው አንመጣም ብለዋል። ም/ቤቱ አጀንዳ አለመላኩ ጦርነት እንዳወጀ ይቆጠራል ብለዋል። አጀንዳ አለመላክ ጦርነት ሲያስነሳ ይህ በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ሊሆን ይሆን?!
ምክንያታዊና በስምምነት የተላለፈውን ምርጫ ከፌደራል መንግሥቱ ውጭ፣ ነጻነትን ከማወጅ ባልተናነሰ እርምጃ በክልሌ ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ የተነሳው ህወሓት ወታደራዊ ሰልፍ ማሳየት እንኳ ሳይቀር ሲደነፋ መክረሙ የሚታወቅ ነው። የፕሮፖጋንዳ ድንፋታው አቋርጦ አያውቅም። በዚህ ድንፋታ ሰለባ የሆኑት አናምናችሁም የሚሏቸው የወልቃይት፣ የጠገዴ የጠለምትና የራያ ነዋሪዎች ተቀዳሚ ናቸው። በገዛ ቀያቸው በአያት ቅድመ አያት እርስታቸው ላይ የሚኖሩ እንደገና ለግድያ፣ ለእስራትና ለስደት እየተዳረጉ ነው። በትውልድም ሆነ አብረው ያልኖሩት የየህወሓት ሹሞች መቀመጫ መቆምያ ነስተዋቸዋል። የህወሓትን ምርጫ የሚቃወሙት የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ባላቸው ጠንካራ የሆነ ኢትዮጵያዊነት ምክንያት እራሳቸውን ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥለው አያዩም። በወያኔ አመራሮች እየተገፋ ያለውን የፖለቲካ መስመር ይቃወማሉ። በምርጫውም ለመካፈል ፍላጎት የላቸውም።
የወልቃይት፣ ጠገዴ ጠለምትና የራይ ነዋሪዎች ህወሓት የሚያክሂደውን የምርጫ ሂደት በመቃወማቸው1/ የልዩ ሓይልና ሚሊሺያ አባሎችን ወደማያውቁት የትግራይ አካባቢ ማዛወር፣ 2/የምርጫ ካርድ ያላወጡትን $500 ብር ቅጣት እና ስድስት ወር እስራት እንዲፈረድባቸው ማድረግ። 3/ሸቀጣ ሸቀጦችን፣ እንደ ስኳር እንዳይገዙ መከልከል። 4/ተሰሚነት ያላቸውን በትግራይ ቴሌቪሽን ቀርበው ድጋፍ እንዲሰጡ ማስገደድ። 5/ በተቃዋሚነት ወደፊት ድምጻቸውን ሊያሰሙ ይችላሉ የተባሉትን እንዲታሰሩ ማድረግ። 6/ጥቂት የማይባሉ ተፈናቅለው ክልሉን ለቅው እንዲወጡ ማስገደድ። በተጨማሪ በተለመደው የወያኔ አፋኞች ታፍነው ተወስደው ይሆናል የሚባሉም የት እንደ ደረሱ ያልታወቁ ግለሰቦችም አሉ።
ይህ በመሆኑ የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን የፌደራሉ መንግሥት እንዲቆጣጠረውና ከእልቂት እንዲያድናቸው እየተማጸኑ ነው። የእነዚህ አካባቢዎች ሕዝብ ለረጅም ጊዜ በቅኝ ግዥ ስር እንደሚኖር ሕዝብ ሆኖ ነው የኖረው። ለዚህ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ የፌደራል መንግሥቱ ሊደርስለት ይገባል። መንግሥት በአስቸኳይ አካባቢውን ተቆጣጥሮ ህዝቡን ከደረሰበት ሰቆቃ እንዲታደግ እንጠይቃለን። ወረራን፣ ግፍን፣ ቅሚያንና ሰቆቃን ባጠቃላይ ኢሰባዊ ድርጊትን አውግዘን ለፍትህ ካልቆምን ለኢሰባዊ ድርጊት የይቀጥል ፍቃድ መስጠት ይሆናልና ህወሓትን ማስቆም አለብን።
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር።
ሕዝብ ሁልጊዜም አቸናፊ ነው።
የጎንደር ሕብረት
Comments