የጎንደር ሕብረት ለጎንደር ተፈናቃዮች አንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር መደበ
- Abebe Gelagay
- Feb 21, 2019
- 1 min read
የካቲት 13 2011 ዓ. ም.(2/20/2019)
የጎንደር ሕብረት ለጎንደር ተፈናቃዮች አንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር መደበ
ባለፉት ወራት በመሃልና በምዕራብ ጎንደር በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ሲዘገብ ሰንብቷል። ቀውሱ በመተማና አካባቢው ሲጀምር መንግሥት ፈጥኖ እርምጃ ባለመውሰዱ ልዩ ልዩ አጀንዳ ያላቸው ታጣቂ ሃይሎች ሁኔታውን በመጠቀም ቀውሱ እንዲባባስ ለማድረግ እድል አግኝተዋል። በዚህም ምክንያት ከመተማ እስከ ጎንደር እና ከጎንደር እስከ ትክል ደንጋይ ከዚያም አልፎ ወደ ሁመራ በሚወስደው መንገድ ሁሉ ችግሩ እንዲባባስ ሆኗል። በዚህም ምክንያት ከ 50000 እስክ 60000 የሚሆኑ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል። በአሁኑ ወቅት በትክል ደንጋይ፣ በአይምባ፣ በወለቃ፣ በመተማ አካባቢና በሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ወደ ሱዳን የገቡ ተፈናቃዮችም እንዳሉ ይነገራል።
የጎንደር ሕብረት ጎንደር ባለው ቅርንጫፍ ቢሮው በኩል ሁኔታውን ሲከታተልና እርዳታ ለማድረስ የፀጥታውን አመችነት ሲለካ ቆይቷል። ከዚህ የተላኩ አባሎቹ ትክል ደንጋይ፣ ወለቃ እና አይምባ በመሄድ ተፈናቃዮችን አናግረዋል። ያሉበትን ሁኔታ ተረድተዋል። ሌሎችንም ተፈናቃዮች አሉባቸው የተባሉትን ቦታዎች ለማየትና የችግሩን መጠን ለማወቅ ጥረቱ ቀጥሏል።
የጎንደር ሕብረት በደረሱት ዘገባዎች ላይ ተመስርቶ ለተፈናቃዮች እርዳታ ለማድረስ አንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር (1,000,000.00) መድቧል። እርዳታውም በአስቸኳይ እንዲደርስ ጎንደር ላለው ቅርንጫፍ መልእክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ መሬት ላይ ባለው ዘገባ ላይ ተመስርቶ እንደሁኔታው የእርዳታውን መጠንም ከፍ ለማደርግ ወስኗል። አባላቱም ሆኑ ደጋፊዎች የወገኖቻችንን ሰቆቃ ለመቀረፍ በሚደረገው ጥረት በስቴት ቅርንጫፎች በኩል ገንዘብ በማሰባሰብ የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንዲያደርጉ ጥሪያችን እናቀርባለን።
የጎንደር ሕብረት ከዚህ በፊት የቤንሻንጉል የወልቃይትና የራያ ወግኖች በተፈናቀሉበት ጊዜ ለነዚህ ወገኖች ፈጥኖ እርዳታ እንዳደረሰ የሚታወስ ነው።
Comments