ግጭት ጠማቂነት በቃ ብለናል!
- gyisma83
- Apr 17, 2024
- 2 min read

ገናና ባለታሪክ በሆነችው ኢትዮጵያ በደም ተጋምዶ የተፈተለን ትውልድ በዘር፣ በጎሳና በጥቃቅን ነገድ ለያይቶ በማካለል አቧድኖ የማገዳደልን የትህነግ መሰሪ ስራ ዛሬም በበኩር ልጁ በተረኛው የዘር መራሹ የብልጽግና መንግሥት ዳግም ቀጥሏል። ደጋግሞ የከሸፈበትን የቅማንትና የአማራ ማህበርን የማካለልና የማለያየት ተግባር አሁንም እንደገና አገርሽቶበታል። በሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የቅማንት ማህበረሰብ አባሎችን መልምሎ ናዝሬት/አዳማ በመውሰድ ለመሪነት አሰልጥኗል። ምንም እንኳ ከሆቴል የማያልፉ ቢሆንም፣ እነዚህን የኦሮሙማ ብልፅግና ምልምል ከሃዲዎችና ይህን ለማስፈፀም በተላላኪነት የሚያገለግሉት የአማራ ብልፅግና መሪዎች ጎንደርን በሌላ ቀውስ በመክተት የፋኖን ትግል እናደናቅፋለን በሚል እየተራወጡ ነው። ሆኖም ‘የአንድነት ዋልታና ምሰሶ’ የሆነው የጎንደር ህዝብ የተለመደውን ምላሽ እንደሚሰጣቸው አንጠራጠርም።
የቅማንት ማሕበርን በማሽበልበል አብሮት ከኖረው የአማራው ማሕበረሰብ ጋር ለማለያየት የተጀመረው ሴራ ቀደም ብሎ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በ1982 የጀመረ ነው። ምንም እንኳ ያለእረፍት ይህን እውን ለማድረግ ያላሴሩት ሴራ፣ ያልወጡት አቀበት፣ ያልወረዱት ቁልቁለት ባይኖርም በሁለቱ ማሕበረሰቦች ጥረት ወያኔ አልተሳካለትም። ለክልል የታሰቡትን የቀበሌ ቁጥሮች እየለዋወጡ፣ አመራር መልምለው ባጀት መድበው ቅማንቱ ማሕበረሰብን ለመለየት እነበረከት ያደረጉት ጥረት ፈቅ አላለም። ይሁን እንጅ ወራሾቻቸውም ደግመው፣ ደጋግመው ከመሞከር አልቦዘኑም።ግን ወሀ ቢወቅጡት እንቦጭ ነውና ባሉበት ማደክደክ እንጅ የትም አይደርሱም።
ሁልጊዜ ከተላላኪነት የማይወጣው የአማራው ክልል በየጊዜው የቅማንትን ማሕበረሰብ እየሰበሰበ ክልላችሁን ውሰዱ ባጀት መድበንላችኋል እያለ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ማሕበረሰቡን ሲወተውት ቆይቷል። የቅማንት ማሕበረሰብ ግን የምትምሩትን ምራችሁ፣ ለፈርድ የሚቀርበውን አቅርባችሁ ጨርሱ፤ እኛ መካለል አንፈልግም ሲል መልሱን ሰጥቷል። ከፌደራሉ መንግሥት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልም ስለሕብረተሰቡ እውቀት ሳይኖራት ጭልጋ ድረስ በመሄድ ምልምሎቿን ወስዳ አዲስ አበባ አሰልጥና የትም ሳትደርስ የጉም ሽታ ሆና ቀርታለች። መቸም ሁለቱን ሕብረተሰብ ለማለያየት ያልቧጠጡት ዳገት የለም። በመከፋፈል የግዛት እድሜየን አራዝማለሁ በሚል በዚህ እኩይ ተግባር የተጠመደው የአማራው ብልፅግና ግን ተስፋ አልቆረጠም። እንደገና፤ ዶ/ር ይልቃል የክልሉ መሪ በነበረበት ወቅት የቅማንት ማሕበረሰብ ወኪሎች ናቸው የሚላቸውን ባሕር ዳር ሰብስቦ ክለላችሁን ውሰዱ ባጀት መድበንላችኋል ሲል ጠይቆ ፍርጥም ያለ፣ መካለል አንፈልግም የሚል መልስ አግኝቷል።
አሁን ደግሞ የኦሮሙማው ብልጽግና ከወያኔ ተቀብሎ ይህንኑ የቅማንት ኮሚቴ የሚባል ከቅማንት ማሕበረሰብ አንዳችም ድጋፍ የሌለው ቡድን በማደራጀትና ከአዲስ አበባ የለቃቀማቸውን ተወላጆች ሰብስቦ ለክልል መሪነት አሰለጥናለሁ እያለ በመውረግረግ ላይ ነው። ይህ ሴራ አሁንም እንደሚከሽፍ ጥርጣሬ የለንም። በስካይላይት ሆቴል በድብቅ ተዶልቶ "የቅማንት ማህበረሰብ ተቆርቋሪ ናችው" በማለት ልዩ ስልጠና የተሰጣቸው በጥቅም የተገዙ ግለሰቦች የተወሰኑ ቀበሌ ገበሬ ማህበራትን ይዘን በቅማንት አስተዳደር የማካለል "ከአዲስ አበባ እና ከአማራ ክልል ይሁንታ አግኝተናል" በማለት በጭልጋ አካባቢ አይከል ከተማ ገብተዋል። ትግሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷልና ካረፉበት ሆቴል እንደማያልፉ ግን እርግጠኛ ነን።
በፋኖ የማያቋርጥ ትግል የተዋከቡትና መቋቋም ያቃታቸው የፌደራሉና የአማራው ክልል መንግሥቶች አሁንም ሁለቱን ማሕበረሰቦች አጋጭተን ፋታ እናገኛለን ብለው እየተፍጨረጨሩ ነው። መርዶ እንንገራችሁና፣ በአሁን ወቅት ከቅማንት ማሕበረሰብ የወጡ ፋኖዎች በሻለቃዎች ተደራጅተው በጭልጋ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ናቸው። ከእንግዲህ ወዲህ ሳምሪን የሚመሩ የቅማንት ኮሚቴ አባላት በመተማ መግባት ቀርቶ፣ ብቅ አይሏትም። ዛሬ የብልፅግና ፓርቲ በተለይም የኦሮሙማው መንግሥት ፀረ ሕዝብ፣ ፀረ ኢትዮጵያ ሴራ ያልገባው የለምና የምትዝናኑበት ቀርቶ የምትረግጡት መሬት የለም።
እነዚህ ሁለት ማሕበረሰቦች በዘር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባህል ተጋምደው የተሰሩና የማይለያዩ ከአንድ እናትና አባት የተወለዱ ልጆች የተለያየ ስም እንደሚኖራቸው ሁሉ እነዚህ ሁለት ማሕበረሰቦችም የተለያየ መጠሪያ ይኑራቸው እንጅ አንድ ናቸው። እንደሚታወሰው የጎንደር ሕብረት አንዳንድ ግጭቶችና አለመግባባቶች ሲነሱ በሽማግሌ እንዲያልቅ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። አሁንም እንዲህ አይነት ሴራዎችን እየተከታተለ በማጋለጥና በባህላችን እንደሚደረገው በወቅቱ የሚነሱ ጉዳዮች መፍትሄ እንዲያገኙ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር የሽማግሌ ሸንጎዎችን በመደገፍ በተቻለው ሁሉ መርዳቱን ይቀጥላል።
ኢትዮጵያ በፅናት ለዘላለም ትኑር!
Kommentare